AMN – ግንቦት 26/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በትዕግሥት በመሰለፍ ያሳዩት ጠንካራ ተሳትፎ እና የታየው ሰላማዊ ድባብ ሕዝቡ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ገልጸዋል።
ታዛቢ ቡድኑ ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራሩን በከፍተኛ ሁኔታ አድንቋል።

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ቡድኑ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ መሰማራቱን አስታውቀዋል።
በምዝገባ ወቅት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መተግበሩ ለመራጮች ቁጥር መጨመር፣ በተለይም ለወጣቶች ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በምርጫው ዕለት የምርጫው አካባቢ በአጠቃላይ ሰላማዊ የነበረ መሆኑን፣ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ መከናወኑን፤ ታዛቢዎች በተመደቡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች በተረጋጋ ሁኔታ አገልግሎት ማግኘታቸው ያለ ምንም እንቅፋት ድምፃቸውን የመስጠት ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የምርጫ አስፈጻሚዎችና የጸጥታ አካላት ከፍተኛ ሙያዊ ብቃትና ዝግጁነት፣ የምርጫ ቦርድ በሂደቱ ላይ ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው ተብሏል።

በሁሉም ታዛቢ በተመደቡባቸው ጣቢያዎች አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ የተሟሉ በመሆናቸው የሎጂስቲክስ ዝግጅቱ በቂ እንደነበር መረጋጋጡንም አመላክተዋል።
የመራጮች ተሳትፎን ለማረጋገጥ ሲባል የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙ፣ መራጮች የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ በመግለጫቸው አብራርተዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ