የውስጥ አካላትን በጥራት የሚያሳየው የሲቲ ስካን ምርመራ እና ማወቅ የሚገባዎት ወሳኝ የጤና ጥንቃቄዎች

You are currently viewing የውስጥ አካላትን በጥራት የሚያሳየው የሲቲ ስካን ምርመራ እና ማወቅ የሚገባዎት ወሳኝ የጤና ጥንቃቄዎች
  • Post category:ጤና

AMN – ሰኔ 1/2018 ዓ.ም

የሕክምና ሳይንስ የደረሰበትን የላቀ ቴክኖሎጂ እና የኤክስሬይ ጨረርን በማጣመር የሰውን የውስጥ አካል በጥራትና በዝርዝር ለማየት የሚያስችለው የሲቲ ስካን (CT Scan) ምርመራ፤ ለበርካታ የጤና እክሎች ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ቅድመ-ምርመራ የማይታለፉ ጥንቃቄዎችን እንደሚሻ ተገለጸ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የክሊኒካል ራዲዮሎጂ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኤፍሬም ፍቃዱ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ስለ ምርመራው አገልግሎት እና በተለይም እርጉዝ እናቶችና የኩላሊት ሕመም ያለባቸው ሰዎች ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ወሳኝ ጥንቃቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሲቲ ስካን እንደ ኤክስሬይ ሁሉ ጨረርን በመጠቀም የሚሰራ የሕክምና ማሽን ሲሆን፣ ምርመራው የኤክስሬይ ጨረርን እና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን በቅንጅት ይጠቀማል።

ማሽኑ የኤክስሬይ ጨረሮችን በተለያየ አቅጣጫ ወደ ሰውነት በመላክ እና በተለያዩ የዕይታ መስመሮች (በአግዢያል፣ በሳጂታል እና በኮሮናል ፕሌኖች) ምስሎችን መልሶ በመገንባት የሰውነትን የውስጥ ክፍል በጥራትና በዝርዝር ለማየት ያስችላል።

ሲቲ ስካን ከሌሎች ምርመራዎች (ከኤክስሬይ እና ከአልትራሳውንድ) የሚለየው ይህንን ባለ ብዙ ገጽታ ምስል የመስጠት አቅም ስላለው ነው።

የሲቲ ስካን ምርመራ ዓይነቶችና አገልግሎቶች

የሲቲ ስካን ምርመራ እንደየ ጥቅሙና እንደ ሕመምተኛው ፍላጎት በተለያየ መልኩ ይታዘዛል። ከእነዚህም መካከል፣ ለደረት የውስጥ ክፍል፣ ጥራት ላለው ዕይታ እንዲሁም በጆሮ ውስጥ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን በትክክል ለይቶ ለማወቅ ይታዘዛል።

የደም ትቦዎችን ሁኔታ ለመከታተል እና ከደም ዝውውር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማየት ያገለግላል። በብዛት የተለመደው ደግሞ እንደ ሕመሙ ዓይነት ለጭንቅላት፣ ለአጥንት፣ ለደረት እና ለሆድ ዕቃ ክፍሎች የሚታዘዙ በርካታ የሲቲ ስካን ዓይነቶች አሉ።

የሲቲ ስካን ምርመራ ወቅት ሊደረጉ የሚገቡ ወሳኝ ጥንቃቄዎች

የሲቲ ስካን ምርመራ በመድኃኒት ታግዞ ወይም ያለ መድኃኒት ሊከናወን ይችላል። ምርመራው በመድኃኒት (ኮንትራስት) ሲታገዝ በሽታው ያለበትን የሰውነት አካል ወይም የዕጢ ሁኔታ ይበልጥ በግልጽና በጥራት ለመለየት ይረዳል።

ለምርመራው የሚሰጡ መድኃኒቶች ከሰውነት የሚወገዱት በኩላሊት በኩል ተጣርተው ነው። ስለዚህ የኩላሊት ችግር ባለባቸው ታካሚዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያመጡ ስለሚችሉ ምርመራው ላይደረግ ይችላል።

ታካሚዎች የኩላሊት ሕመም ካለባቸው ለሕክምና ባለሙያው በግልጽ መናገር ይኖርባቸዋል፡፡ ማንኛውም ዓይነት አለርጂ ያለባቸው ሰዎች አስቀድመው ለባለሙያው ማሳወቅና መጠንቀቅ አለባቸው።

ሲቲ ስካን ጨረርን የሚጠቀም ማሽን በመሆኑ ለጽንስ ጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል።

በመሆኑም፤ ማንኛዋም እናት በውስጧ እርግዝና እንዳለ ካወቀች ወይም ጥርጣሬው ካላት ከምርመራው በፊት ለሕክምና ባለሙያው የግድ መናገር አለባት።

ምርመራው እጅግ አስፈላጊና አግባብነት ያለው ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው የሚከናወነው፤ ካልሆነ ግን ምርመራው ጨረር በሌላቸው እንደ አልትራሳውንድ ወይም በኤም አር አይ ምርመራዎች እንዲተካ ይደረጋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review