ከመሠረተ ልማት እስከ ዘላቂ ልማት የዘለቀው የኢትዮጵያ ከተሞች ለውጥ

You are currently viewing ከመሠረተ ልማት እስከ ዘላቂ ልማት የዘለቀው የኢትዮጵያ ከተሞች ለውጥ

AMN – ሰኔ 4/2018 ዓ.ም

ከለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ከተሞች የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት እና ማህበራዊ ለውጥ ዋና ማማዎች እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረጉ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

መንግስት ከተሜነትን እንደ አንድ የልማት አቅም በመመልከት፣ የከተሞችን የመኖሪያ፣ የኢኮኖሚ እና የመሠረተ ልማት አቅም ለማሳደግ ጥረቶችን እያደረገ ነው።

ከለውጡ ማግስት በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚስተዋለው ለውጥ የከተማ ውበት ግንባታ ነው። በተለይም በአዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የተከናወኑት ታላልቅ ፕሮጀክቶች የከተሜነትን ጽንሰ-ሀሳብ ወደ ስነ-ምህዳራዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር ቀይረውታል።

ከተሜነትን ዘላቂ ለማድረግ በመሠረተ ልማት ላይ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው። የከተማ ውስጥ የመንገድ አውታሮች፣ የድልድዮች እና የትራፊክ ፍሰትን የሚያሻሽሉ ግንባታዎች የከተማዎችን ዋና ዋና መንገዶች በማስፋት፣ ምቹ የእግረኛ መንገዶችን፣ የመብራት እና የውበት ስራዎችን በማካተት የሀገሪቱን ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው።

በተለይ አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን እና የከተሜነት ገጽታዋን ለማዘመን የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ ዘመናዊ የቢሮ ግንባታዎች እና የመስተንግዶ ስፍራዎች እየተከናወኑ ነው። ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዘመናዊ አዳራሾች እና ሆቴሎች እንዲስፋፉ እየተደረገ ነው።

የኮሪደር ልማት እና አዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ያሉ ፕሮጀክቶች ከተማዋን በለሙ አረንጓዴ ቦታዎች፣ መናፈሻዎች እና የብስክሌት መሄጃዎች ለማስዋብ የከተሜነት መገለጫ ሆነዋል።

የከተማ አስተዳደር አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ መስጠት እና የከተማ ትራፊክ ቁጥጥርን በካሜራ እና በቴክኖሎጂ ማዘመን።

ለዲፕሎማቲክ ተቋማት እና ለነዋሪዎች ፈጣን የሆነ የኢንተርኔት እና የመገናኛ አገልግሎት አቅርቦትን ማሻሻል እና የከተማዋን ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶች የሚያንፀባርቁ ሙዚየሞች እና የኪነ-ጥበብ ማዕከላት እድሳት እና ግንባታ መስፋፋት፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በሪል ስቴት ልማት አማካኝነት የከተማዋን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች ከግዜ ወደ ግዜ እየተጠናከሩ መጥተዋል።

ዘመናዊ የኤሌትሪክ አውቶቡስ አገልግሎት ማስፋፋት፣ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰትን የሚያቀሉ የመንገድ ማቋረጫዎች እና ለዜጎች ምቹ በርካታ ተርሚናሎች፤ የከተማውን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ እየተሰሩ ይገኛሉ።

ከለውጡ ወዲህ፣ እንደ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ እና መቀሌ ያሉ ከተሞች የራሳቸው የከተሜነት መለያዎች እዲኖራቸው ተሰራ ሲሆን ፤ጎንደር ፣ጂጂጋ፣ አፋር ባሉ ከተሞች ሐይቅ ዳርቻ እና የከተማ መሰረተ ልማት ስራዎችን በአጭር ግዜ ውስጥ በመስራት ለቱሪዝም ምቹ በማድረግ፣ የሆቴል እና የመዝናኛ ተቋማትን በማስፋፋት የከተሜነት መገለጫዎች እየተፈጠሩ ነው።

ከተሞች የኢንዱስትሪ፣ የንግድ እና የአገልግሎት ማዕከላት እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ይህም በከተሞች የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለከተሜነት እድገት የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

የከተማ አስተዳደሮች አገልግሎታቸውን ዲጂታይዝ በማድረግ ለዜጎች ፈጣን እና ግልጽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ በመሶብ የአንድ መዓከል አገልግሎት እጠሰሩ ናቸው።

የዘመናዊ ከተሜነት አንዱ መለኪያ የሁሉም ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ነው። ከለውጡ ወዲህ የተከናወኑ የከተማ ልማት ስራዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ የመንገድ ዳር ንግድን በዘላቂነት የሚያስተናግዱ እና ለወጣቶችና ለሴቶች የስራ እድልን የሚፈጥሩ መሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶባቸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review