AMN – ሰኔ 06/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሀገር አቀፍ የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም እያካሄደ ይገኛል።
ፕሮግራሙ “የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ያመሰግናሉ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሰለጠነ የፖለቲካ ሽግግር ያለንን ተነሳሽነት ያሳየ ነው ብለዋል።
ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ተዓማኒና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ የሰለጠነ የፖለቲካ መገለጫ መሆኑንም አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ኢትዮጵያውያን የመረጥነው ነጋችንን በካርዳችን ወስነን፣ የዘመነችና የሰለጠነች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ለእኛ ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመዘኛና ማረጋገጫ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታየ፤ ብርድና እና ፀሐይ ሳይበግረን መትጋታችን በተለይ በክፉና በተሳሳተ መንገድ ለሚመለከቱን ሁሉ የገዘፈ መልዕክት እንዳለው አስገንዝበዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖለቲካ በስሜትና በጭፍንነት የሚመራ አለመሆኑን ያረጋገጠ፣ በብስለትና በአስተዋይነት ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል።
በምርጫው አሸናፊ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በአስተዋይነት ለሕዝብ የተገባውን ቃል የመተግበርና የኢትዮጵያን ሕልውና የማስጠበቅ አደራ እንደተጣለባቸውም አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸውን ለተወጡ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ተሳትፎ ላበረከቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ የሕዝብና የሀገርን ጥቅም ለማስከበር የሚሠራው ምክር ቤቱ፣ 55 የማህበረሰብ ድርጅቶች ከ10 ሺህ በላይ በሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር ምርጫውን መታዘባቸውን ተናግረዋል።
በማጠቃለያውም ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በንጉሡ በቃሉ