ከዘመናዊው ዓለም ዴሞክራሲ የቀደመ ታሪክና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት እና የሥልጣን ሽግግር

AMN ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ጥንታዊ፣ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው በዓለም አቀፍ የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ የዲሞክራሲ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ መዋቅር ነው።

ይህ ሥርዓት የሰላም፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የአካባቢ ጥበቃ እሴቶችን ያቀፈ ነዉ፡፡

በገዳ ሥርዓት ውስጥ አንድ ወንድ በህይወት ዘመኑ የሚያልፍባቸው አምስት ዋና ዋና የእድሜ እርከኖች አሉ። እያንዳንዱ እርከን ሰምንት ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን፣ አጠቃላይ የአንድ ዑደት የስልጣን ዘመን 40 ዓመት ይወስዳል።

ዋናዎቹ የእድሜ እርከኖች ደበሌ ፣ ጋሜ ፣ ኩሳ ፣ ራባ ዶሪ እና ገዳ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ከ40 ዓመት በኋላ ያሉት ግለሰቦች ወደ ዩባ እና ጉዶማ ደረጃዎች የሚሸጋገሩ ሲሆኑ እነዚህ የሽማግሌዎች ምክር ቤት (አማካሪዎች) ሆነው ያገለግላሉ።

የኦሮሞን የገዳ ሥርዓት እጅግ አስደናቂ የሚያደርገው የስልጣን ሽግግር ሂደቱ ሲሆን ስልጣን የሚተላለፈው በሰላማዊ፣ በዲሞክራሲያዊና ፍጹም በሆነ ስነ-ስርዓት ነው።

አንድ የገዳ መሪ (አባ ገዳ) ስልጣን ላይ የሚቆየው ለ8 ዓመታት ብቻ ሲሆን ጊዜው ሲያበቃ ለአንድ ቀንም ቢሆን ስልጣን ማራዘም እንደማይፈቀድ የኦሮሞ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ባሊ “Baallii ” ማለት የስልጣን ምልክት (በትር) ፡ ስልጣን ማስረከብ “Baallii kennuu” ሲባል፣ ስልጣን መቀበል ደግሞ “Baallii fudhachuu” ተብሎ ይታወቃል፡፡የስልጣን ሽግግሩ የሚከናወነው ኦዳ ዛፍ ስር ሲሆን ኦዳ የነፃነት፣ የሰላምና የፍትህ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

የኦሮሞን ገዳ ሥርዓትና የሥልጣን ርክክብ የበለጠ ዘመናዊ የሚያደርገው የሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ ያስረከበዉ አባ ገዳ የማይገለል መሆኑ ነው፡፡ ይልቁንም ወደ ዩባ አማካሪነት በመሸጋገር አዲሱን መሪ በምክርና በዕውቀት ይረዳል።

በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ውስጥ ዋቃ እና ሰፉ የሞራል ልዕልናን የሚገልጹ ሲሆኑ ዋቃ ፈጣሪን የሚገልጽ ነው፡፡ ሥርዓቱ በፈጣሪ ፊት እውነትንና ፍትህን ማስፈንን እንደ ትልቅ ግዴታ ይቆጥረዋል።

ሰፉ ስነ-ምግባር፣ እርስ በርስ መከባበር፣ ተፈጥሮን አለመበከል እና ህግን ማክበር ሲሆን ሰፉን የጣሰ ሰው ከማህበረሰቡ እስከመገለል ሊደርስ ይችላል።

የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ያለ ደም መፋሰስ ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ ማጋራት፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር የሚያስተምር ቀደምት የዲሞክራሲ እሴት መሆኑን የኦሮሞ ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡

ከዘመናዊው ዓለም ዴሞክራሲ የቀደመ ታሪክና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት እና የሥልጣን ሽግግር ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ተጽእኖዎችን ተቋቁሞና ጸንቶ ዛሬ ላይ የደረሰ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የህዝቡን ባህልና እሴት በጠበቀ ሁኔታ በደመቀ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የቱለማ ኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የ71ኛው ዙር የስልጣን ሽግግር ‘ዳካ ኮራ’ በተባለ ልዩ ስፍራ የተካሄደ ሲሆን ባለፉት ስምንት ዓመታት በሜልባ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ሲመራ የነበረው የቱለማ ገዳ ስልጣኑን ለገዳ ሙደና አባገዳ ጌቱ ተሊላ ቱፋ አስረክቧል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በርካታ እንግዶች የታደሙ ሲሆን ይህም ከዘመናዊው ዓለም ዴሞክራሲ የቀደመ ታሪክና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የሥልጣን ሽግግር ለአዲሱ ትዉልድ ለማውረስና ሥርዓቱን ለማጠናከር ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review