AMN ሰኔ 8/2018

ውይይቱ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የቀድሞ ታጣቂዎቹ አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ የሚያስረክቡም ይሆናል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመድረኩ እንደገለጹት፣ ወጣቶች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ያሏቸውን ጥያቄዎች በአጀንዳ መልክ ቀርጸው ወደ ሀገራዊ ምክክሩ ማምጣታቸውን አድንቀዋል።

ጥያቄዎችን ይዞ ወደ ምክክር መምጣት፣ ለችግሮች በጋራ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ትልቁን በር እንደሚከፍትም ገልጸዋል።
የትኛውም ፍላጎትና ጥያቄ በመሳሪያ ሳይሆን በውይይት፣ በመነጋገርና በመመካከር መግባባት ላይ የሚደረስበት መሆኑን ወጣቶች ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ማረጋገጥ የሚቻለው መሳሪያ ይዞ ጫካ ውስጥ በመግባት የወጣትነት እድሜን መስዋዕት በማድረግ ሳይሆን፣ የሀገሪቱን ችግሮች በፊት ለፊት ውይይትና ምክክር በጋራ በመፍታት መሆኑን አንስተዋል።

የኮሚሽኑ ዋና ዓላማም ለማንም ወገን አድሎ ሳይደረግ፣ ሁሉም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ሀሳብ ለሀሳብ እንዲመካከሩ በማድረግ ለችግሮች ዘላቂ እልባት መፈለግና በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት የሰላም ጉዳዮች አማካሪ ብርጋዴር ጄነራል ኃይሉ ጎንፋ በበኩላቸው፣
የትኛውንም አጀንዳ በሰላማዊ መንገድ በመደማመጥ መፍታት መቻል ትልቅ እሴት መሆኑን አብራርተዋል።
ማህበረሰቡ በየትኛውም ሁኔታ ሰላም እንዲደፈርስ አይፈልግም ያሉት ብርጋዴር ጄነራሉ፣ ልጆቹ ከነፍጥ ይልቅ የሰለጠነ ፖለቲካን እንዲለማመዱ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
የሰላም መንገድ ሁሉንም አሸናፊ በማድረግ ወጣቶች የነገዋን ሀገር ለመገንባት አሻራቸውን የሚያሳርፉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ ዓይነቱ በምክክር ላይ የተመሰረተ አካሄድ ትልቁ የትግል ማዕቀፍ መሆን እንደሚገባ በማንሳት፥ ሀገራዊ ፋይዳውም የላቀ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።