የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ዜጎች በቅንነትና በሃላፊነት ስሜት ሊሳተፉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ

You are currently viewing የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ዜጎች በቅንነትና በሃላፊነት ስሜት ሊሳተፉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ

AMN – ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር፣ አለመግባባቶችን እና ልዩነቶችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚያስችል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሀገሪቱ ያሉ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ የሀገራዊ ምክክሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ያነጋገራቸው ወ/ሮ ሚስጥረ ሚካኤል፤ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ከትልልቅ እስከ ትንንሽ ያሉ ልዩነቶች በቅን ልቦናና በምክክር ይፈታሉ ብለዋል፡፡

እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክርም አለመግባባቶችን እና ልዩነቶችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

ይህም ልጆቻችን ተቻችለው እንዲያድጉ የሚያደርግና ኢትዮጵያንም ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግራት መሆኑን በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ሀገራዊ ምክክርም ጥሩ ነገር እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ሚስጥረ አክለውም፣ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን በሁሉም አካባቢ የሚገኘው ዜጋ ልቡ መልካምና ቅን መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን ለመፍታት ለሀገራዊ አንድነት በጋራ መስራት እና ችግሮችን ተወያይቶ ለመፍታት እያንዳንዱ ዜጋ ዝግጁ መሆን እንዳለበት የገለጹት ደግሞ አቶ አብዱበሽር አሊ ናቸው፡፡

አለመግባባቶችን በጊዜው ተቀራርቦ መፍታት አስፈላጊ ስለመሆኑም በማንሳት፣ በምክክር ብዙ ነገሮችን ማስተካከል እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አየነው ይርሳው በበኩሉ፤ የቆዩ ችግሮቻችንን ተነጋግረን መፍታትና በልማት ስራዎች ላይ በንቃት መሳተፍ ይኖርብናል ብሏል፡፡

ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት በጋራ መምከር እንዳለባቸው የጠቆመው ወጣቱ፣ ይህም ተስማምቶና ተቻችሎ ለመኖር እንዲሁም ሀገርን ለመገንባት ያግዛል ሲል ገልጿል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review