አርሰናል ቪኒሺየስ ጁኑዮርን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀመረ

You are currently viewing አርሰናል ቪኒሺየስ ጁኑዮርን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀመረ

AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም

አርሰናል ቪኒሺየስ ጁኒዮርን ከሪያል ማድሪድ ለማስፈረም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተዘገበ።

በዝውውር ዘገባው ተዓማኒነትን እያዳበረ የመጣው ዘ አትሌቲክ ላይ የሚፅፈው ዴቪድ ኦርነስቴይ መረጃውን ቀድሞ አጋርቷል።

ብራዚላዊው የመስመር አጥቂ በሪያል ማድሪድ ያለው ውል ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ ይቀረዋል። ከስፔኑ ክለብ ጋር ያለውን ቆይታ የሚያረጋግጥ ውል ይፈርማል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን እውን አልሆነም።

ማድሪድ በቀጣይ የውድድር ዓመት ተጫዋቹን በነፃ ላለማጣት ሊሸጠው እንደሚችል ተገምቷል። የስፔኑ ክለብ ኮትዲቯራዊውን ያን ዲዮማንዴ ለማስፈረም ለላይብዚግ ጥያቄ ማቅረቡ የቪኒሺየስ ቆይታ ላይ እርግጠኛ አለመሆኑን የሚያሳይ ተደርጎ ተቆጥሯል።

አርሰናል ፍላጎቱን ቢያሳይም ከሪያል ማድሪድ ጋር ምንም ዓይነት ይፋዊ ንግግር ባይጀምርም ፣ የአርሰናል ከፍተኛ ሃላፊዎች ግን የ26 ዓመቱን ብራዚላዊ የማስፈረምን እቅድ ሙሉ ለሙሉ ስለመቀበላቸው ተዘግቧል።

አርሰናል በግራ መስመር አጥቂነት ሞርጋን ሮጀርስን ቀዳሚ ተመራጭ አድርጎ ቢንቀሳቀስም ተጫዋቹ ለቼልሲ ፈርሟል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን ዋንጫ ማንሳት ይፈልጋል። ለዚህም የማጥቃት ሚናውን የሚወጡ ተጫዋቾች ጥራት ለማሳደግ ወስኗል።

ቪኒሺየስ በማድሪድ ያለው ሁኔታ አርሰናል ምናልባት ለበርካቶች ማሰብ የሚከብደውን ዝውውር ለመፈፀም እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል። ቪኒሺየስ ጁኒዮር ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው እ.ኤ.አ በ2018 ከሀገሩ ክለብ ፍላሚንጎ ነበር። ስምንት ዓመት በሞላው የማድሪድ ቆይታው 375 ጨዋታዎችን አድርጎ 128 ግቦችን ሲያስቆጥር ፤ 100 ግብ የሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review