AMN- ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም
ሀገራዊ ምክክሩ በውይይትና በመግባባት ለሀገሪቱ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ብቸኛና አዋጭ መንገድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ገለጹ።
ዋና ኮሚሽነሩ የጉባኤውን አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ ሂደቱ ከማንኛውም ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ በገለልተኝነት እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከህዝብና ከተለያዩ አካላት የተሰበሰቡ ከሁለት ሺህ በላይ አጀንዳዎች፣ ሂደቱን ውጤታማና የተቀናጀ ለማድረግ ወደ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች እንዲሰበሰቡ መደረጉን ዋና ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።
እያንዳንዱን አጀንዳ በሙሉ ተሳታፊ ለማወያየት ከሁለት መቶ ቀናት በላይ የሚፈጅ በመሆኑ፣ ሀገሪቱ ካላት የጊዜና የበጀት አቅም አንጻር ሂደቱን በቡድን ከፍሎ የማወያየት ዘዴ እንደተመረጠም ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በየቡድኑ ጥልቀት ያለው ውይይት ከተደረገ በኋላ፣ የሁሉም ቡድኖች ተወካዮች በጋራ በመወያየት የመጨረሻ መግባባት ላይ እንደሚደርሱ ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ደረጃ በደረጃ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገሩን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ውይይቱ በንዑስ ቡድኖች ተጀምሮ ወደ 50 አባላት ወዳሏቸው ቡድኖች እንደተሸጋገረ አስረድተዋል።
በቀጣይ ቀናትም ወደ 250 እና በመጨረሻም 500 አባላት ባሏቸው ትላልቅ ቡድኖች ደረጃ እንደሚካሄድ አብራርተዋል።
በተሳታፊዎች አደረጃጀት ወቅት በመጀመሪያ ላይ የተወሰኑ ክፍተቶች ታይተው እንደነበር የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በባለሙያዎችና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ክፍተቶቹ በፍጥነት መስተካከላቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ውክልና ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል።
ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ሃይማኖት በሌላው ላይ ጫና እንዳያሳድር እና ሂደቱ ወደ አንድ ወገን እንዳያዘነብል ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተሳታፊዎች የቆየውን የመከባበርና የመደማመጥ ባህል በመጠበቅ በነጻነት ሀሳባቸውን እያንሸራሸሩ እንደሚገኙም ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።
በበረከት ጌታቸው