ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ የማስተላለፍ ፈቃድ ያልተሰጣቸውን 17 ህገ-ወጥ አስተላላፊ ድርጅቶችን ስም ይፋ አደረገ

AMN – ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም

May be a graphic of text

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ያልተሰጣቸውን 17 ህገ-ወጥ አስተላላፊ ድርጅቶችን ስም ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሠረት አዱሊስ መኒ ትራንስፈር፣ አማል ኤክስፕረስ፣ አማል ዩኤስኤ፣ አማና ኤክስፕረስ፣ አቫንቲ፣ አዋሽ ዳይሬክት፣ ባካል መኒ ትራንስፈር፣ ጁባ ኤክስፕረስ፣ ራስሚ ፔይ፣ ረማድ ፔይ (ወይም ረማዳ ፔይ ካህ)፣ ሽጌይ መኒ ትራንስፈር፣ ታጅ ፋይናንሻል ሰርቪስ፣ ታሳ ፔይ፣ ተወከል መኒ ሰርቪስ፣ ዩኤስ ዋየር ፣ ወርልድ ዳይሬክት ሊንክ እና ዞላ የተሰኙ ድርጅቶች ሕጋዊ ፈቃድ እንደሌላቸው ገልጿል።

የእነዚህ ድርጅቶች ህገ-ወጥ ተግባራት በኢትዮጵያ ሕግ በጥብቅ የተከለከሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወጣው መግለጫ፤ ኅብረተሰቡ፣ የዳያስፖራ አባላት እና ደንበኞች ፈቃድ የሌላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎች እና ሕገ-ወጥ የሐዋላ መረቦችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

በህገ-ወጥ መንገዶች ገንዘብ መላክም ሆነ መቀበል ደንበኞችን ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ፣ ለክፍያ መዘግየት፣ ለባንክ ሒሳብ ዕገዳ እንዲሁም ለሕግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል በመግለጫው አስጠንቅቋል፡፡

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የገንዘብ ዝውውር እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ ዜጎች ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውን የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶችን ብቻ ሊጠቀሙ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

ህገ-ወጥ መንገዶችን መጠቀም ላኪዎችንም ሆነ ተቀባይ ቤተሰቦችን አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ለአስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል አስገንዝቧል።

በተጨማሪም ደንበኞች ገንዘባቸው ደኅንነት እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ መድረሱን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸውን የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪሎች ብቻ እንዲጠቀሙ መክሯል።

ለዚህም ማንኛውንም የገንዘብ ዝውውር ከማድረግ በፊት፣ የተመረጠው አስተላላፊ ድርጅት ሕጋዊ ስለመሆኑ በባንኩ ይፋዊ ድረ-ገጽ https://nbe.gov.et/mta/ በመግባት ማረጋገጥ እንደሚቻልም ባንኩ አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review