
በሙዚቃ ጉዞው ውስጥ የአገር ባህልና ማንነትን ከዘመናዊ የሙዚቃ አቀራረብ ጋር በማጣመር ለአድማጮቹ የተለያዩ ሥራዎችን አበርክቷል።
ከታወቁት የሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል “ደንደሾ”፣ “ያድሴ”፣ “ባሌ ሮቤ ” “ኑደሬ ጋሞ ጎፋ”፣ “ዱማ ዱሜ”፣ “ሎሽኬ” እና “ሎላሼ” ይገኙበታል።
በተለይ “ደንደሾ” የተሰኘው ሥራ ስሙን በሰፊው እንዲያስተዋውቅ ካደረጉት ዋነኛ ሥራዎቹ መካከል ሲሆን፣ በኋላ የተለቀቁት ሥራዎችም በሙዚቃ ጉዞው ውስጥ ያለውን ተወዳጅነት አጠናክረዋል።
አስጌ በግል ሥራዎቹ ብቻ ሳይወሰን ከተለያዩ የሙዚቃ አርቲስቶች ጋር በመተባበርም ሰርቷል። “ዞኖ ዞካ” ከቤቲ ጂ፣ “አኩኩሉ” ከማይኮ እና “ማሄላንዶ” ከእፀገነት ኃይለማርያም ጋር ካደረጋቸው የጋራ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ። እንዲሁም “ሰዋዊ” በተሰኘው የጋራ ሙዚቃ ሥራ ከማህሙድ አህመድ፣ ታደለ ገመቹ፣ ሰለሞን ኃይሌ፣ ራሄል ጌቱ እና ሌሎች አርቲስቶች ጋር ተሳትፏል።
የአስጌ የሙዚቃ ተሳትፎ በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በCoke Studio Africa በመሳተፍ ከኡጋንዳዊቷ ድምፃዊት Sheebah ጋር የሙዚቃ ስራ ሰርተዋል። ይህም የኢትዮጵያን የሙዚቃ ባህልና የራሱን የሙዚቃ አቀራረብ ከሌሎች የአፍሪካ የሙዚቃ ባህሎች ጋር ለማገናኘት ያደረገውን ጥረት ያሳያል።
በሳቂታነቱ፣ በቀልድ ችሎታውና በተፈጥሯዊ የመዝናኛ አቀራረቡ የሚታወቀው ድምፃዊ አስጌ፣ አሁን ደግሞ ለተመልካቾች አዲስ ሳቅና መዝናኛ ይዞ ሊመጣ ነው።
“ጤንነትዎን እንሸልም” በሚል መልዕክት በአዲሱ ዓመት በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ከሚጀምሩት አዳዲስ ፕሮግራሞች መካከል “እንቁዎች” አንዱ ሲሆን፣ አስጌ በዚህ አዲስ የመዝናኛ ጉዞ ውስጥ የራሱን ልዩ ቀለም ሊያክል ነው።
የአስጌን ሳቅ፣ ቀልድና አዲስ የመዝናኛ አቀራረብ ለመመልከት፣ “እንቁዎች”ን በአዲስ አመት በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ይጠብቁ!