የመደመር መንግስት የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲመራ ይፈልጋል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN -ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

የመደመር መንግስት የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲመራ እንደሚፈለግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ከዓመታት በፊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የህዝብ ቅሬታ ከሚስተዋልባቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ ነበር።

አሁን ግን ታሪክ ተቀይሯል። በዓመት የማይስተናገድ ዜጋ ጉዳዩን በቀን ውስጥ ፈፅሞ የሚመለስበት ተቋም ሆኗል። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ይገኛል።

ዛሬ በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተን እንደተመለከትነው፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቋማዊ ሪፎርምና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎች የተቋሙን ስምና የሥራ ባህል በአዲስ መልክ እየቀየሩ ነው ብለዋል።

በተለይም አገልግሎቶቹን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ማሸጋገሩ ተገልጋዮች ፈጣን፣ ግልጽና እንግልትን የቀነሰ አገልግሎት እንዲያገኙና እርካታቸውም እንዲጨምር እያደረገ ይገኛል።

አገልግሎቱ በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ራሱን በማደራጀት የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት፣ የቪዛ፣ የጉዞ ሰነዶች፣ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲሁም የአየርና የመሬት ድንበር ቁጥጥርን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን በውጤታማነት እያከናወነ እንደሆነም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

እያንዳንዱ ሪፎርም የሚለካው ዜጎች በሚያገኙት የአገልግሎት ጥራት፣ በሚቆጥቡት ጊዜና በሚያገኙት እርካታ ነው። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋማዊ ለውጥም መንግሥት ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂና ዜጋ-ተኮር የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል።

በቀጣይም የተቋሙን የዲጂታል ሽግግር በማፋጠን፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ጥራትን በማሳደግ፣ ተቋማዊ ዐቅሙን በማጠናከር እና የተገልጋዮችን እርካታ በተጨባጭ በማረጋገጥ ላይ መትጋት ይገባል። የተገልጋዮችን ሐሳብና ቅሬታ ራስን ለማሻሻል መነሻ አድርጎ መቁጠር ከተቻለ ከዚህም በላይ መለወጥ ይቻላል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review