AMN- ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በብሔር፣ በሃይማኖትና በባህል ኅብር ያጌጠች ባለብዙ ቀለም ድንቅ ሀገር ናት።
ይህ ብዝኃነቷ የውበቷን ያህል የጽናቷና የጥንካሬዋ ምስጢር በመሆኑ የዓለምን ትኩረት የሳቡ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች።
ይህንኑ ድንቅ ሀገራዊ ዕሴት ይበልጥ ለማጎልበትና የተገመደውን የአብሮነት ዕሴት ለማጠናከር ጳጉሜን 4 ቀን የኅብር ቀን ተብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል፡፡
ዕለቱ ኢትዮጵያውያን በትውልዶች መካከል በፅኑ መሰረት ላይ በገነቡት የወል ትርክት፣ የጋራ እሴቶችና ውብ ባህሎች አማካኝነት ያሳኳቸውን ታላላቅ የድል ታሪኮች የሚያስታውሱበትና አዲሱን ዘመን በተስፋ የሚቀበሉበት ነው።
ትናንት በልጆቿ የጋራ ክንድ በዓድዋ ተራሮች ላይ የነጻነትን ታሪክ በወርቅ ቀለም የጻፈችው ኢትዮጵያ፤ ዛሬም ያንኑ የማይበገር አብሮነት በመጠቀም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማሳካት የማንሰራራትና የሕዳሴዋን ብስራት እውን እያደረገች ትገኛለች።
የዕለቱ ዋና ዓላማ፤ የሀገሪቱን የብዝኃ ውበት፣ የህዳሴና የጋራ እድገትን ማፋጠኛ በማድረግ በሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ይበልጥ ማጠናከር ነው።
ቀኑን ምክንያት ማድረግም በሀገር አቀፍ ደረጃ አብሮነትን፣ መከባበርንና ሀገራዊ ፍቅርን የሚያጎሉ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እየተካሄዱ ነው፡፡
በበረከት ጌታቸው