የተደረገልን የማዕድ ማጋራት ድጋፍ የሰብአዊነት ከፍታ ማሳያ ነው- ማዕድ ተጋሪዎች

AMN – ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያደረገላቸው የማዕድ ማጋራት ድጋፍ የሰብአዊነት ከፍታ ማሳያ መሆኑን የማዕድ ተጋሪዎች ገለጹ።

የኑሮ ጫና ከብዶቸው፣ ጧሪና ደጋፊ አጥተው በነበሩበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያደረገላቸው የማዕድ ማጋራት ድጋፍ ትልቅ መጽናኛ ሆኗቸዋል።

ይህ መልካም ሥራ «ሰው አለኝ» የሚል ትልቅ የመጽናኛ ስሜት የፈጠረላቸውና ማኅበራዊ ትስስራቸውን ያጠናከረ ታላቅ የርኅራኄ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ በጎነትን በንቅናቄ ብቻ ሳይሆን በተቋም ደረጃ መምራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።

የአዲስ አበባ ሕብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ጎን ለጎን፣ በከተማዋ የኑሮ ጫና ላለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ ለኤ.ኤም.ኤን እንደተናገሩት፤ መርኃ ግብሩ ዓመቱን ሙሉ ከሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ በክረምት ወራት የኑሮ ጫና ያለባቸውን ዜጎች ለመደገፍ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን አስረድተዋል።

ከለውጡ ወዲህ መደጋገፍ እና መረዳዳትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች መሠራታቸውን የሚናገሩት የማዕድ ተጋሪዎች በበኩላቸው፤ ያለ ምንም ልዩነት እንደ ሀገር ተሳስቦ የሚኖርበት ሁኔታ መፈጠሩ አርአያነት ያለው ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሌላው ተጠቃሚ የታመሙና እና የኑሮ ጫና ያለበቸውን ወገኖች ቤታቸው ድረስ በመሄድ ማዕድ ማጋራታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል፡፡

በከተማ ደረጃ የዜጎችን ማኅበራዊ ትስስር በማጠናከር፣ ችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ድጋፍ በመስጠት እና የመተሳሰብ እሴትን ከፍ በማድረግ ረገድ ይህ የበጎ ፈቃድ ሥራ ትልቅ አርአያ እንደሚሆን ተመላክቷል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review