አዲስ አበባን ስሉጥ ከተማ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

AMN- ጳጉሜን 5/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ “ተፈጥሯዊ አእምሮን ከዲጂታል ፈጠራ ጋር ያጣመረ የነገ ትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ ጳጉሜን 5 “የነገ ቀን”ን አክብሯል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በቴክኖሎጂ ትግበራ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በፋይናንስ ሥርዓት፣ በጤና እና በመሬት ሀብት አስተዳደር መሠል ዘርፎች አበረታች ውጤቶች የተገኙ ሲሆን፤ ይህም አዲስ አበባ ለወጠነችው የስሉጥ ከተማነት (Smart City) ጉዞ ጠንካራ መሠረት እየጣለ ይገኛል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ፤ የከተማዋ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ባዘጋጀው የ”የነገ ቀን” መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂ የነገዋ ኢትዮጵያ መልክ ነው።

አዲስ አበባ በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ባከናወቻቸው ሥራዎች ስኬታማ አፈጻጸሞች እየተመዘገቡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አብርሃም፤ በመፍጠር፣ በመፍጠን እንዲሁም በመዝለል መርህ አዲስ አበባን ከቀሪው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ስሉጥ አዲስ አበባን የመገንባት ሂደት በልዩ ትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬትና የ2030 ውጤታማ ትግበራ ለዚህ ማሳያ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ረጅሙን የድህነት ዘመን ወደ ኋላ በመተው አዲስ አበባን ወደተሟላ የዲጂታል ዘመን ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር)፤ አዲሱን የቴክኖሎጂ ዘመን በንቃት በመቀበል የከተማዋን ሁለገብ ሕዳሴ ለማብሰር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ቢሮው ጳጉሜን 5 “የነገ ቀን”ን በፓናል ውይይት፣ በጉብኝት እና ለአዳዲስ ፈጠራ ባለቤቶች እውቅና በመስጠት በድምቀት አክብሮ ውሏል።

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review