AMN- መስከረም 16/2019 ዓ.ም
የመስቀል ደመራ በዓልን በደመቀ እና በተቀናጀ መልኩ እንድናከብር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያደረገልን ድጋፍ ከፍተኛ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደመራ በዓልን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በታላቅ በድምቀት እያከበረች ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ መስቀል የእርቅ፣ የሰላም እና የታላቅ ድል መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በመልእክታቸው፣ ይህን ታላቅ በዓል በዚህ ደረጃ በደመቀ እና በተቀናጀ መልኩ እንድናከብር የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል ብለዋል።
በተለይም የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት፣ ለመስቀል እና ለሌሎችም በዓላት አከባበር የሚያስፈልገውን እገዛ በማድረግና ወጪን በመሸፈን አስተዳደሩ ልዩ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከበዓላት አከባበር ባለፈ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ የሚደነቅ ትብብር እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ለተደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍም በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በበዓሉ ታዳሚያን ስም ምስጋናቸውን የገለጹ ሲሆን በዓሉ የሰላም፣ የእርቅ እና የፍቅር ይሁንልን ሲሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ