የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ በማኀበረ-ኢኮኖሚ መስኮች ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ አጋር ነው፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም

የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ በማኀበረ-ኢኮኖሚ መስኮች ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ አጋር ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሩ የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ በማኀበረ-ኢኮኖሚ መስኮች ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሰራ እና በተለይም በልማት ትብብር፣በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ግንኙነቱን ለማስፋት ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአምባሳደሯ በቀጣናው ስላለው ወቅታዊ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር በበኩላቸው በአዲስ አበባ 22 የሕብረቱ አባል አገራት ተወካዮች እንደሚገኙ እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ጉልህ ስትራቴጂካዊ ሚና አኳያ ሕብረቱ ከአገሪቱ ጋር ላለው ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ከ180 በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች እንደሚገኙ በመጥቀስ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኩባንያዎች የበለጠ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ገንቢ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review