ከሳርቤት አደባባይ-መካኒሳ-ፉሪ ሀና በመገንባት ላይ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የስራ ሂደት ገምግመናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ኅዳር 22/2017 ዓ.ም

ከሳርቤት አደባባይ- መካኒሳ-ፉሪ ሀና በመገንባት ላይ የሚገኘውን 18 ኪ.ሜ የሚሸፍነውን የኮሪደር ልማት የስራ ሂደት መገምገማቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ 18 ኪ.ሜ የሚሸፍነው ይህ የኮሪደር ልማት ስራ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል የሚያስችል እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የመንገድ ደረጃውን ማሻሻል፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች፣ የህጻናት መጫዎቻዎች፣ ሰፊ የእግረኛ መንገድ፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የታክሲና አውቶቡስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ግንባታቸዉ ሳይጠናቀቅ የቆዩ ህንጻዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት የማስገባት እና ነባር ህንፃዎችን የማደስ ስራዎችን ያካተተ መሀኑንም ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ ከተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በተጨማሪ የንፋስስልክ ላፍቶ ክፍለከተማም ማህበረሰቡን በማስተባበር ተጨማሪ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ እና ይህም በአቃቂ ቃሊቲ ከተጀመረው ጋር የሚገጥም እንደሚሆን አመላክተዋል።

በዛሬው ጉብኝታቸው አንዳንድ ቅሬታ የቀረበባቸዉ ጉዳዮችን በቦታዉ በመገኘት ከባለ ጉዳዩቹ ጋር ተመካክረው መፍታታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ስራው በፍጥነት እና በጥራት እንዲከናወን ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም እየደገፉ ያሉ ማህበራትን እና የአካባቢውን ነዋሪዎችም አመስግነዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review