AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ/ም
ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ ከንግድ ትርፍ ባለፈ፣ ከሀገራዊ ህልውና፣ ከዲጂታል ሉዓላዊነት እና ከመረጃ ደህንነት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑን የዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ዕጩ የሆኑት ጌታቸው ታደሰ ገለጹ።
መምህር ጌታቸው ታደሰ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የባህር በር ያላት ሀገር ብትሆንም፣ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተፈጠረ “ሰው ሰራሽ” ምክንያቶች የባህር በር አልባ ሆና እንድትቆይ ተደርጓል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሀገሪቱን በሁለንተናዊ መልኩ ለከፍተኛ አደጋ እና ጥገኝነት ዳርጓታል።
እንደ ምሁሩ ትንታኔ፣ የባህር በር አለመኖር በንግድ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የዲጂታል ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋት ደቅኗል።
የመረጃ ጠለፋ ስጋት፡ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች በጎረቤት ሀገራት በኩል ማለፋቸው፣ የኢትዮጵያን የመረጃ ልውውጥ ሙሉ በሙሉ በሀገሪቱ ቁጥጥር ስር እንዳይሆን አድርጎታል።
የንግድ ምስጢር ጥበቃ፡ የንግድ ሂደቶች እና የመረጃ አደረጃጀቶች በሌሎች ሀገራት መተላለፊያ ላይ ጥገኛ መሆናቸው፣ ስልታዊ የሆኑ የንግድ ምስጢሮች ለሌሎች ወገኖች እንዲጋለጡ በር ይከፍታል።
በኢኮኖሚው ረገድ የወደብ አልባነት የሚያስከትለው ኪሳራ በዜጎች ኪስ ላይ በቀጥታ ተፅዕኖ እንዳለው ጌታቸው ታደሰ አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም የኢትዮጵያን ምርቶች ከኬንያ ናይሮቢ ጋር ሲያነጻጽሩ፣ በኢትዮጵያ ቢያንስ የ30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ጠቅሰው፣ ይህም የሀገሪቱን የገበያ ተወዳዳሪነት ከመጉዳቱም በላይ ለዋጋ ግሽበት እና ለኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ ምሁሩ ገለፃ ፣ የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ “የመኖር እና አለመኖር” የህልወና ጉዳይ ነው። የውጭ ሀገራት የኢትዮጵያን መግቢያ እና መውጫ መቆጣጠራቸው ሀገራዊ ስትራቴጂን ለማስፈጸም ያዳግታል ባይ ናቸው ፡፡
መንግስት በአሁኑ ወቅት የደረቅ ወደቦችን፣ የሎጅስቲክስ ቀጠናዎችን እና የባቡር መስመሮችን በማጠናከር ወጪን ለመቀነስ የሚሰራቸው ስራዎች የሚደነቁ ቢሆኑም፣ ዘላቂው መፍትሄ ግን የራስ የወደብ ባለቤት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም ሰላም ወሳኝ መሆኑን መምህር ጌታቸው አስረድተዋል። ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆኗ በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ሽብርተኝነትን ለመግታት እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስርን እና የንግድ ደህንነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አወንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የባህር በርን ለማግኘት የምትከተለው የ”ሰጥቶ መቀበል” እና የቀጠናዊ ትስስር ዲፕሎማሲ ትክክለኛ መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ፣ ጉዳዩ በህግም፣ በታሪክም ሆነ በተፈጥሮ ኢትዮጵያ የሚገባት መሆኑን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች እንደገለጹት፣ የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ቁልፍ ማነቆ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ይህ ጉዳይ እውን እስኪሆን ድረስ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ እና ለሀገር ሉዓላዊነት ዋነኛው መሰረት መሆኑን ዕጩ ዶክተር ጌታቸው ታደሰ ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ አስገንዝበዋል፡፡
በያለው ጌታነህ