ህዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግና የጸጥታ ተቋማትን በማቀናጀት በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ተችሏል

You are currently viewing ህዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግና የጸጥታ ተቋማትን በማቀናጀት በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ተችሏል

AMN- ግንቦት 11/2018 ዓ.ም

ህዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግና የጸጥታ ተቋማትን በማቀናጀት በተከናወነው ስራ በአዲስ አበባና በሸገር ከተማ አስተዳደሮች ዘላቂ ሰላምን ማስፈን መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተማ አስተዳደሮች የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የጸጥታ ዘርፍ ቅንጅታዊ ሥራዎች አፈጻጸምን በጋራ እየገመገሙ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ቅንጅታዊ ሥራዎች ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባቸው እና የደህንነት ስጋት የሌለባቸው ከተሞችን መፍጠር መቻሉን የገለጹት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤ ለዚህ ስኬት ህዝብን ባለቤት ያደረገና የጸጥታ ተቋማትን ያቀናጀ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ሥራ መከናወኑ የላቀ ሚና እንደተጫወተ አስረድተዋል።

ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሰውን “የሰላም ሰራዊት” እንዲሁም በሸገር ከተማ ደግሞ “ጋቸና ሲርና” የተባሉትን ህዝባዊ አደረጃጀቶች በምሳሌነት አንስተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለይም ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን ከመከላከል አኳያ አበረታች ሥራ መከናወኑን የገለጹት ኃላፊዋ፤ የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ ግንባታን፣ እንዲሁም ሐሰተኛ ሰነዶችንና የብር ኖቶችን የመሳሰሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን መከላከል ተችሏል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከተሞቹን ኢላማ ያደረጉ የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ተልዕኮ በማክሸፍ ረገድ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ ባለፉት 8 ዓመታት ላስመዘገበቻቸው ስኬታማ የልማት ሥራዎች በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ከተሞች የኢንቨስትመንትና የልማት ማዕከል እንዲሆኑም የቅንጅታዊ ጸጥታ አስተዳደር ሥራው አበርክቶ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም፣ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ይህ ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመራሮቹ በጋራ አረጋግጠዋል።

በሄኖክ ዘነበና በበላይሁን ፍስሐ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review