ለሃገራዊ መግባባት እንቅፋት የሆኑ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን በመታገልና የዘመናት ስብራቶቿን በምክክር በመፍታት ለሃገራዊ መግባባት ምቹ መደላድልን እየፈጠረች የምትገኘዉ – ኢትዮጵያ

You are currently viewing ለሃገራዊ መግባባት እንቅፋት የሆኑ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን በመታገልና የዘመናት ስብራቶቿን በምክክር በመፍታት ለሃገራዊ መግባባት ምቹ መደላድልን እየፈጠረች የምትገኘዉ – ኢትዮጵያ

AMN ግንቦት 18/2018 ዓ.ም

ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነጻነት ተምሳሌት ሆና የምትጠቀሰዉ ኢትዮጵያ ለድህነቷ መንስኤ ናቸዉ ተብለዉ ከሚነሱ አንኳር ስብራቶች መካከል አንዱ ሃገራዊ መግባባትን መፍጠር አለመቻሏ ነዉ፡፡

የሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ስክነት የጎደለዉና መግባባት የተሳነዉ በመሆኑ ሃገሪቱ በምታከናዉናቸዉ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን ያህል ረጅም የሃገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ የሌላቸዉ አንዳንድ የዓለም ሃገራት፤ ብሄረ መንግስትና ሃገራዊ መግባባትን መፍጠር በመቻላቸዉ በአጭር ዓመታት ዉስጥ ከፍተኛ ኢኮኖሚ መገንባት ችለዋል፡፡

እነዚህ ሃገራት ከምንም በላይ ልዩነቶችን አክብሮ ለአንድ ሃገራዊ ጥቅም በጋራ መቆም የሚችል ማህበረሰብ መገንባት ችለዋል፡፡

የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነችዉ ኢትዮጵያም በሃገራዊ ጥቅሞች ላይ የማይደራደር ጠንካራ ህዝብ ያላት ብትሆንም ብዝሃነትን ተቀብሎ ፤ የዉስጥ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በምክክርና በንግግር መፍታት የሚችል የሰለጠነ ማህበረሰብ በሚፈለገዉ መንገድ መገንባት አልቻለችም፡፡

ከሁሉም በላይ ባለፉት ዓመታት በሁለት መንገድ የተቀነቀኑት ሃገራዊ እና አካባቢያዊ ማንነቶች ማንንም አሸናፊ ማድረግ ካለመቻላቸዉም በላይ በልማት እና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆነዉ ዘልቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸዉ ማንነት፤ ሃይማኖት፤ ባህል፤ ቋንቋና መሰል እሴቶች ቢኖራቸዉም ይህንን ልዩነት አክብሮ በጋራ ከመኖር ይልቅ አንዱ ሌላኛዉን ለመጨፍለቅና ለመጠቅለል የተሄደበት መንገድ ልማትን ከማደናቀፉም በላይ የሰላም እጦት ዋንኛ መንስኤ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በተለያየ ጽንፍ የቆሙ ሁለቱን ማንነቶች ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ለአመታት ሲነገሩ የነበሩ ነጠላ ትርክቶችም የሃገራዊ መግባባት ዋንኛ እንቅፋት ከመሆን አልፈዉ የህዝቦችን አብሮ መኖር በተደጋጋሚ እስከመፈተን ደርሰዋል፡፡

ላለፉት በርካታ አመታት በተለይ ብሄርና ሃይማኖትን መሰረት አድርገዉ በተለያዩ መንገዶች ሲነገሩ የነበሩ የተዛቡ፤ ሃሰተኛና ከፋፋይ ትርክቶች በተሟላ መንገድ ብሔራዊ መግባባት እንዳይፈጠር እንቅፋት ከመሆናቸዉም በላይ እስከ ዛሬ ድረስ እነዚህን የተዛቡ፤ ሃሰተኛና ከፋፋይ እሳቤዎችን ለማረም የሚቸገሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቂት አይደሉም፡፡

ያለፉት መንግስታዊ ሥርዓቶችም ቢሆኑ ከፋፋይና ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች ለህዝቡ አብሮ መኖር፤ ለልማትና ለዘላቂ ሰላም ዋንኛ ተግዳሮት መሆናቸዉን ተገንዝበዉ ስብራቱን ለማከምና ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሄዱበት ርቀት ዉስን ነዉ፡፡

ሃገራዊ ለዉጡን ተከትሎ በተለያዩ አጀንዳዎች የሚስተዋሉ መካረሮችን ለማቀራረብና ለማስቀረት፤ እንዲሁም በመተሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር በተሰሩ በርካታ ስራዎች የጋራ ትርክትን ለመገንባት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግስት መጽሃፋቸዉ፤ መንግስት ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ወደ መሃል በማምጣት፤ የሃሳብ ትግል እንዲኖር ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር፤ ፖለቲካዊ ልዩነቶች በንግግርና በምክክር እንዲፈቱ ምቹ መደላድልን በመፍጠርና እና የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትን ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የለዉጡ መንግስት ለዘመናት ያልተፈቱ የሃገሪቱ ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ያደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ በተካሄዱ የምክክር መድረኮች ህብረተሰቡ እንደ ወንድማማች ህዝብ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ልዩነቶቹን ለመፍታት ፍላጎት ማሳየቱ ሃገራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚቻል በተግባር አስመስክሯል፡፡

በሃገር ዉስጥና በተለያዩ የዉጭ ሃገራት የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ነፍጥ አንስተዉ ጫካ ገብተዉ ሲታገሉ የነበሩ ኃይሎች ሳይቀሩ ሰላማዊ መንገድን መርጠዉ ከመመለሳቸዉም ባሻገር የሃገራዊ ምክክሩ ሂደት ተሳታፊ ሆነዉ እንዲፈቱላቸዉ የሚፈልጓቸዉን አጀንዳዎች በነጻነት ማቅረባቸዉ ኢትዮጵያ ከረጅም አመታት በኋላ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በትክክለኛዉ መንገድ ላይ ስለመሆኗ በቂ ማሳያ ነዉ፡፡

የለዉጡ መንግስት የተለያዩ የፍትህ ተቋማትን በማቋቋም ጭምር ለረጅም ዘመናት የተከማቹና ያልተፈቱ ስብራቶች እንዲታከሙ ከሚያደርገዉ ጥረት ጎን ለጎን መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ተቋማት የግጭትና ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ ከፋፋይ፤ አግላይ እና ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን እንዲታገሉ ምቹ መድረኮችን በመፍጠር ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ዛሬ ላይ ጽንፈኛ፤ ዘረኛ፤ ከፋፋይ እና ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን የሚጸየፍ፤ ብዝሃነትን፤ ህብረብሔራዊ አንድነትን፤ አብሮነትን፤ ወንድማማችነትን እና መከባበርን የሚገነዘብ ትዉልድ እየተገነባ መሆኑም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርም ሆነ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ ትልቅ ዋስትና ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ባልተለመደ መልኩ ፖለቲካዊ ልዩነቶች በጦር መሳሪያ አፈ ሙዝ ሳይሆን በንግግርና በምክክር እንደሚፈቱ የተገነዘቡ አንዳንድ የታጠቁ ሃይሎች ከግጭትና ከጦርነት ይልቅ በሰለማዊ መንገድ ለመታገል ወስነዉ ወደ ቀዬአቸዉ መመለሳቸዉና የተሃድሶ ስልጠና ወስደዉ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ትልቅ መሰረት መጣሉን የሚያበስሩ ናቸዉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review