AMN – ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሙስሊሞች ታላቁን የእስልምና ሃይማኖታዊ በዓል የሆነውን እና የመሰዋዕት በዓል በመባል የሚታወቀውን ዒድ አል-አድሃን አክብረዋል።
በዓሉ ነቢዩ ኢብራሂም ለአላህ የነበራቸውን ታማኝነት እና ታዛዥነት ለመግለጽ ልጃቸውን ለመሰዋት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ይዘከርበታል።
ዒድ አል-አድሃ በሳውዲ አረቢያ ከሚከናወነው ዓመታዊ የሐጅ ስነ-ስርዓት ጋርም የጠበቀ ትስስር እንዳለው ነው የሚነገረው።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ኢስያ ባሉ በርካታ አካባቢዎች በአል አድሃ በዓል አከባበር ላይ ተሳትፈዋል።
በእየሩሳሌም በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ምዕመናን ለዒድ ሰላት በአል-አቅሳ መስጂድ መሰብሰባቸውን አልጃዚራ ዘግቧል።
የዒድ ሰላት ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ኦማን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኢራቅ፣ ግብፅ፣ ፍልስጤም እና ሶሪያን ጨምሮ በ11 የአረብ ሀገራት ተካሂዷል።

በሰላቱ ላይ መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን፥ ለሰላም፣ ለአገራዊ መረጋጋት እና ለፍልስጤም ድጋፍ የሚጠይቁ ጥሪዎች ተስተጋብተዋል።
በአፍሪካም ሱዳን ፣ ኬንያ ና ናጄሪያ በመሳሰሉ ሐገራት በድመቀት መከበሩ ነው የተዘገበው።
በቱርክ በዓሉ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ መስጂዶች በማለዳ በተደረጉ የዒድ ሰላቶች መከበሩን አናዶሉ ዘግቧል።
በአዘርባጃን ምዕመናን በዋና ከተማዋ ባኩ በሚገኙ መስጂዶች በመሰብሰብ ለሀገራቸው እና ለመላው የእስልምና ዓለም ሰላምና ብልጽግናን ተመኝተዋል።

በባኩ በሚገኙ መስጂዶች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የታየ ሲሆን፥ መስጂዶቹ መላውን ሰጋጅ ማስተናገድ ባለመቻላቸው ምዕመናን በአደባባዮች፣ በጓሮዎች እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ሰላታቸውን አድርገዋል።

ካዛክስታን እና ኪርጊስታንን ጨምሮ በማዕከላዊ እስያ ሀገራት የሚገኙ ሙስሊሞች የዒድ አል-አድሃ ሰላትን በመስጂዶች ውስጥ ሰግደዋል።
ቦስኒያ-ሄርዞጎቪና፣ ሰርቢያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ክሮኤሺያ፣ ሰሜን መቄዶንያ፣ አልባኒያ እና ኮሶቮን ጨምሮ በባልካን ሀገራት የሚኖሩ ሙስሊሞችም የዒድ አል-አድሃ በዓልን በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል።
ታደሠ ሽፈራው