AMN- ግንቦት 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ 8ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ይህ ዘመናዊ ማዕከል የተገነባው ለዜጎች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ሲሆን፣ ሕዝቡ በአካል መጥቶ ከመስተናገዱ ባለፈ ባለበት ቦታ ሆኖ በቴክኖሎጂ የታግዘ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላዋል፡፡
ማዕከሉ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለዓመታት የዘለቀውን አድካሚ የእንግልትና የቢሮክራሲ ሰንሰለት ሙሉ በሙሉ የሚበጥስ ሲሆን፤ በማዕከሉ የቲን ቁጥር ማውጣት፣ የመንጃ ፈቃድ ማደስ፣ የልደት ሰርተፍኬት የመሳሰሉና ለሌሎች አገልግሎቶችና መስፈርት የሚባሉ ሰነዶችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።

ምቹና ጽዱ ሆኖ የተገነባው ማዕከል ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መተላለፊያ ያለው ሲሆን፣ በማዕከሉ የሚሰሩ እናቶችና ወጣት ሠራተኞች በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ሕፃናት ልጆቻቸው የሚቆዩበት፣ የሚጫወቱበትና የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበት ልዩ ሥፍራ ነው።
ይህ ዘመናዊ ማዕከል በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች፣ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች እጅ የተገነባ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ መሶብ የብልጽግናችን ማዕድ በመሆኑ ወደዚህ ማዕከል መጥቶ የሚጎድል ነገር አይኖርም ብለዋል።
በአዲሱ ማዕከል ውስጥ ለህዝብ አገልግሎት መስጠትን በተመለከተ ያብራሩት ከንቲባ አዳነች፤ አዲሱ አሠራር ሰነፎችን የሚቀጣ፣ ትጉሃንን ደግሞ የሚያበረታታ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ስራቸውን በቅንነትና በትጋት ለሚወጡ ሰራተኞች እንደ ስራቸው ልክ በየጊዜው የደረጃ ዕድገትና ሽልማት ይጠብቃቸዋል ያሉት ከንቲባዋ፤ ሆን ብሎ ሰውን የሚያንገላታ፣ በስራ ሰዓት የማይገኝ እና የተቀመጠውን የአገልግሎት ደረጃ የማያሟላ ሰራተኛ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር እንደሚዘረጋም አብራርተዋል።
ተገልጋይን በክብርና በፈገግታ ማስተናገድ አሁን መብት ሳይሆን የውዴታ ግዴታ ወይም ግልጽ ህግ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው