አዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያሳየችው ለውጥ አስደናቂ ነው- የውጭ ጎብኚዎች

You are currently viewing አዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያሳየችው ለውጥ አስደናቂ ነው- የውጭ ጎብኚዎች

AMN- ሰኔ 1/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በከተማ ልማት፣ በአረንጓዴ ፕሮጀክቶች፣ በወንዝ ዳርቻ ማስዋብ እና በኮሪደር ልማት ሥራዎች አስደናቂ ለውጥ በማሳየት የዓለም አቀፍ አድናቆትን እየተጎናጸፈች ነው።

ሰፋፊ መንገዶች፣ የእግረኞች መሄጃዎች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ ዘመናዊ የውሃ ማስወገጃ ሥርዓቶች እና የአረንጓዴ ገጽታ ማስዋቢያዎች የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ ቀይረውታል።

ይህም አዲስ አበባን ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ይበልጥ ምቹና ማራኪ እንድትሆን አድርጓታል።

በቅርቡ ከተማዋን የጎበኙ የውጭ እንግዶች ለውጡን በከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባን እንደጎበኘች የምትገልጸው ጎብኚ፣ ከተማዋ እጅግ ዘመናዊና ውብ ናት ያለች ሲሆን፣ በተለይ ለሕጻናትና ለእግረኞች ምቹ ተደርገው የተሰሩትን ልማቶች አድንቃለች።

ሌላኛዋ ጎብኝም አዲስ አበባ በአረንጓዴ ቦታዎች፣ በሕዝብ መዝናኛ ማዕከላት፣ በህጻናት ፓርኮች እና በወንዝ ዳርቻ ልማቶች ያሳየችው እድገት ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት እንደሚያደርጋት ገልፃለች።

ከተማዋ በአረንጓዴ ቦታዎች፣ በመዝናኛ መሠረተ ልማቶች እና በባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማድረጓን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያዩ ጊዜያት መግለፃቸው ይታወሳል።

ይህም አዲስ አበባ እንደ አፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ ያላትን ቦታ የበለጠ ለማጠናከር የታለመ መሆኑም ተመላክቷል።

ዛሬ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ለውጥ፣ አረንጓዴ ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከዘመናዊ እቅድ ጋር ተጣምረው በአፍሪካ ከሚታዩ ታላላቅ የከተማ መልሶ ማልማት ምሳሌዎች አንዷ ሆና ብቅ እንድትል አስችሏታል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review