AMN – ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያ ሕዝብ እራሱን ከሀሰተኛ መረጃዎች እንዲጠብቅ እና በኮሚሽኑ ላይ ሙሉ እምነትቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ፣ ሐምሌ 8 የተጀመረውን ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔን አስመልክቶ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ ነው፡፡
ኮሚሽኑ የመናገር ነጻነትን ሙሉ በሙሉ የሚያከብር ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችንና ውይይቶችን የሚቀበል ቢሆንም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይታለል አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ይገደዳል ብሏል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው ያለው ኮሚሽኑ የዚህ ሂደት ስኬት የሚወሰነው ዜጎች በትዕግስት፣ በጥበብ እና በጋራ የኃላፊነት ስሜት ለመሳተፍ በሚያሳዩት የጋራ ቁርጠኝነት ላይ ነው ሲል ገልጿል።
ይህም እየተከናወነ ይገኛል ፣ ሂደቱ ተጀመረ እንጂ ውጤቱ ገና ነው፡፡ ይህንን ውጤት በትዕግስት መጠበቅ ደግሞ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠበቅ ይሆናል ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኮሚሽኑ ባወጣቸው የአሰራር ሂደቶች መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
ባለፉት አራት ቀናት ኮሚሽኑ የጉባኤው ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ማድረግን ጨምሮ ለሂደቱ ጠቃሚ በሆኑ የእውቀት እና የስነ-ልቦና ዝግጅቶች እንዲያደርጉ መደላድሉን መፍጠሩንና ይህም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አንድ አካል መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ አብራርቷል፡፡
ይህ እየሆነ ባለበት አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኮሚሽኑ ምክክሩን ለመጀመር እክል እንደገጠመው የተሳሳተ መረጃ ሲያሰራጩ ተመልክተናል ብሏል፡፡
በመሆኑም መሰል የተሳሳቱ መረጃዎች የራሳቸው ዓላማ ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ስለሚችሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየእለቱ የሚኖሩ የምክክር ሂደቶችን ኮሚሽኑ ከሚሰጣቸው መግለጫዎችና የምክክሩን ሂደት ለመዘገብ በስፍራው ከተገኙ መገናኛ ብዙኃን ብቻ በመከታተል ራሱን ከተሳሳቱ መረጃዎች በመጠበቅ የምክክሩን ሂደት እንዲደግፍ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡