ከምስክር ወረቀት ባለፈ የሚሰሩ እጆችንና ሀሳብ የሚያፈልቁ አእምሮዎችን እንፈጥራለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ከምስክር ወረቀት ባለፈ የሚሰሩ እጆችንና ሀሳብ የሚያፈልቁ አእምሮዎችን እንፈጥራለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ለወጣቶች ሰፊ የእውቀትና የክህሎት እድል የሚያስገኝ፣ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ዘመናዊ የስማርት ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄዷል፡፡

ይህ ዘመናዊ ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከሰዎች ለሰዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ትብብር የሚገነባ መሆኑ ተገልጿል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ወጣቶችን በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ ከማሰልጠንና ሰርተፊኬት ከመስጠት ባለፈ፣ በራስ መተማመንን የሚያጎለብት፣ የተግባር ክህሎትን የሚያስታጥቅ እና ሀሳብ የሚያፈልቁ አእምሮዎችን የሚቀርጽ የፈጠራ ማዕከል ይሆናል።

ከንቲባዋ አክለውም፣ ሀገርን ማልማትና ከድህነት መላቀቅ በንድፈ-ሀሳብ ብቻ በተገደቡ ትምህርቶች ሊሳካ እንደማይችል ገልጸው፣ ኮሌጁ ለአገልግሎት ሲበቃ ወጣቶችን ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት፣ ከንድፈ-ሀሳብ ደግሞ ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የክህሎት ድልድይ ይሆናል ብለዋል።

ይህ የስማርት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ አውቶሞቲቭ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በኮሙኒኬሽ እና በቴክስታይል ዘርፎች ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወጣቶች ጊዜያቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከማባከን ይልቅ፣ ነቅተውና ተግተው እነዚህን የተመቻቹ እድሎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶች አእምሮአቸውና እጃቸው ተጣጥመው ለነገዋ ኢትዮጵያ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እራሳቸውን ተጠቃሚ አድርገው ለትውልድ የሚሻገር ሥራ እንዲሰሩ እድሎች በሰፊው መከፈታቸውንም አብራርተዋል።

የረጅም ጊዜ የልማት አጋር ለሆነው ከሰዎች ለሰዎች ድርጅት፣ መሬታቸውን ለለቀቁ አርሶ አደሮች፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።

የማዕከሉን ዘላቂ አገልግሎት ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት በቅንጅት መስራታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አደራ ብለዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review