የኢትዮጵያ ብዝኃ ሃይማኖታዊ እሴቶች የሀገራዊ መግባባት ድልድዮች ናቸው

AMN – ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሃይማኖታዊ እሴቶች የሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫና ሀገራዊ መግባባት ድልድዮች መሆናቸውን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ሲካሄድ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት ፣ ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀች፣ ብዝኃ እምነቶች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር ናት።

የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊ ድምቀትም ሀገራቸውን በዓለም ላይ የአንድነትና መተሳሰብ የዘመናት ድምቀትና የወል ሃብት መገለጫ እንድትሆን ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሃይማኖቶች መካከል ዘመናትን የተሻገረው ትስስርና ጥልቅ መስተጋብርም የሀገርን ሉዓላዊ ዳር ድንበር በማስጠበቅ መስዋዕትነት መክፈልን የሚጨምር የአብሮነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች የሰላም፣ የአንድነትና ምክክር መንፈሳዊ አስተምህሮ መገለጫዎች ናቸው ያሉት ጸሐፊው፣ የእምነት አባቶችም ይህን እሴት በማስቀጠል የሀገራዊ መግባባት ድልድይ ሊገነቡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሁሉም ሃይማኖቶች የእርስ በርስ መስተጋብራቸውን በማጠናከር ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና አንድነት በማስጠበቅ፣ ሕብረ ብሔራዊነትን እንደ ጌጥና ልዩ ፀጋ የሚቆጥር ትውልድ ማፍራት የሚያስችል መሠረት እየተጣለ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን መዳከም የሚሹ የጥፋት ኃይሎችንም እኩይ ሴራቸውን በቅጡ በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላምና አንድነት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review