የትምህርት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች አጥጋቢ ውጤት አምጥተዋል – ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)

AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ የትምህርት ፕሮጀክቶችን እውን ማድረጉን የከተማዋ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው 33ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ፣ በመዲናዋ ያለፉትን የትምህርት ስትራቴጂዎችን በማሻሻል በአዲስ ስትራቴጂ የሚመራበት ዓመት መሆኑ የዘንድሮውን ጉባኤ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት ተረባርበን በሰራንባቸው የትምህርት ዘርፎች ላይ ውጤት ተመዝግቧል ያሉት የቢሮ ኃላፊው ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) ፣ በዚህም የተማሪዎች ውጤት ላይ ፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ እና የአመራሩና የትምህርት ባለሙያው የጋራ ውህደት የተረጋገጠበት ሆኗል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ የትምህርት ፕሮጀክቶችን እውን ማድረጉን ገልጸው ፣ በዚህም በትምህርት ዘርፍ ውጤት እየመጣ ይገኛል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመዲናዋ ቀደም ሲል በደረጃ 4 ምንም የመንግስት ትምህርት ቤት ባልነበረባቸው አካባቢዎች ጭምር አሁን ላይ 23 ትምህርት ቤቶች መድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከቀዳማይ ልጅነት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ የሰጠው ትኩረትና እያከናወነው ያለው ተግባር ለዘርፉ ሰፊ የቤት ስራ የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ፤ የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና የበለጠ ከፍ ለማድረግ የሁሉም አካል ርብርብ እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።

ይህ ጉባኤ በቀጣይ በትምህርቱ ዘርፍ ለሚከናወኑ ተግባራት በርካታ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑም ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)

አብራርተዋል።

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review