በመዲናዋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመጨረስ ብቃት ጨምሯል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት አቅዶ፣ በፍጥነት በመጀመር በፍጥነት የመጨረስ ብቃት ጨምሯል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ 5 ዓመታት ዕቅድ እና የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ ውይይት ማጠቃለያ ላይ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የመጨረስ ብቃት መጨመሩን አንስተዋል፡፡ የቀጣይ እቅድ ከሃገራዊ ራዕይ እና ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ከተቀመጡ እሳቤዎች ጋር በማናበብ መታቀዱንም አስረድተዋል።

አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን የሚል ራዕይ ይዘናል ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህም ሂደት ውስጥ መግባቱን እና ውጤቶችም መታየታቸውን አንስተዋል፡፡

ህዝቡ ከድህነት የመውጣት፣ የማደግ እና የመልማት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መጨረስ ብክነትን ያስወግዳል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የስራ ባህል እየዳበረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተቋማዊ ብቃትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሥራት መቻል፣ እንቅፋቶችን እና ችግሮችን ወደ ድል የመቀየር ልምድ፣ ስራዎችንም በጥራት በመስራት ወደ ውጤት የመቀየር ልምድ አዳብረናል ሲሉም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review