AMN- ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም
ከጊዜ ወደ ጊዜ ገጽታዋ እየተቀየረ፣ የፅዳቷና የዘመናዊነቷ ታሪክ በየመድረኩ የሚነገርላት አዲስ አበባ፤ ከለውጡ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማያቋርጥ አድናቆትና የክብር አክሊሎችን እየተጎናፀፈች ትገኛለች።
የኮሪደር ልማቱ አዲስ ውበት የዘራባት ከተማዋ፤ ለእግረኛና ለብስክሌት ተጓዦች ሰፊ መንገዶችን በመክፈት፣ አረንጓዴ ሽፋኗን በማሳደግ እና የትራፊክ ፍሰቷን በማሳለጥ የአፍሪካ ምርጥ ስማርት ከተሞች ሽልማትን አግኝታለች።
በከተማዋ እምብርት የነበሩ መንደሮችን ገጽታ በማዘመን የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ ውብ የህዝብ መዝናኛ በመቀየር የተከናወነው ተግባርም ከተማዋን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የፅዳትና የአየር ንብረት ጥበቃ አርአያ አድርጓታል።
የዚህ ታላቅ ጉዞ ሌላኛው ምዕራፍ ደግሞ ለነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት የተዘረጋው የፍቅርና የእንክብካቤ እጅ ነው።
የቀዳማይ ልጅነት እድገት ማዕቀፍ ላይ በተሰራው ሥራ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፉ Act For Early Years ኢኒሼቲቭ “የቅድመ ልጅነት እድገት ሻምፒዮን” ተብለው እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ይህ የክብር እውቅና አዲስ አበባን ለአፍሪካ ሕፃናት መጻኢ እድል ብሩህ አምባ አድርጓታል።
ባለፉት ዓመታት ከኮሪደር ልማት እስከ ስማርት ትራንስፖርት፤ ከፅዱ ጎዳናዎች እስከ ሕፃናት እንክብካቤ እና በአረንጓዴ ልማት በቅንጅትና በቁርጠኝነት የተሰራው ሥራ ለሀገር ውስጥ ዜጎች ተስፋ፣ ለውጭ ሀገራት ደግሞ ተሞክሮ ሆኖ ቀጥሏል።
አዲስ አበባ ዛሬ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የከተሞች ትራንስፎርሜሽን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች።
በበረከት ጌታቸው