AMN- ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም የቀጣዩ አድማስ የ3 ዓመት ስትራቴጂ 2ኛ ዓመት የሥራ ዕቅድን ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የ2019 በጀት ዓመት የሥራ እቅድን አስመልክቶ እንደገለጹት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞን እያፋጠነ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም አላማው በዲጂታል የበቃች፣ ፈጠራ የታከለባት፣ ኢኮኖሚዋ የተነቃቃ ኢትዮጵያን መገንባት ነው፡፡
ለሶስት ዓመት ይተገበራል በሚል የተጀመረው የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በስኬት ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ሊሸጋገር መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አንስተዋል፡፡
የቀጣዩ አድማስ የ3 ዓመት ስትራቴጂ ደንበኞች ተሞክሯቸው የላቀ እንዲሆን፣ ደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እና የቴሌኮምና የዲጂታል መሰረተ ልማቶች እንዲሰፉ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም ገቢን ከማሳደግ ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ መሰረተ ልማት ለመገንባት፣ የሰውን ህይወት የሚያቀልና የሚያዘምን ነው ብለዋል፡፡
በቴሌኮምና በዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ በሶስት ዓመት ውስጥ 3 ሺህ 228 ተጨማሪ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት የቀጣዩ አድማስ የ3 ዓመት ስትራቴጂ ዋነኛ ግቡ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ሃገርን በዲጂታል ለማስታጠቅ፣ ለማብቃት እንዲሁም ኑሮን ለማዘመን እና ህይወትን ለማቅለል፣ ለዜጎች አዳዲስ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ብሎም ሁሉም ማህበረሰብ የዲጂታል አገልግሎትን ማግኘት እንዲችል እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የሻምበል ምህረት