AMN -ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ግድቡ እውን እንዲሆን የሞራል፣ የገንዘብ፣ የጉልበት እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፍ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የዕውቅና መርሃ-ግብር እያካሄደ ይገኛል።
የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከድህነት እና ከእርዳታ ጠባቂነት ለመላቀቅ በራሷ አቅም በአባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል።

ባለፉት 14 ዓመታት የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ባለቤት በመሆን ያደረጉት ያልተቋረጠ ድጋፍ ግድቡን ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ አድርጎታል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድል የሀገራችን ሕዝቦች ሁሉ ገድል ውጤት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጽናትና በመደጋገፍ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ለአላማው መሳካት ላሳየው ቁርጠኝነት የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው፤ ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተረባርበው ያለምንም ብድርና እርዳታ በራስ አቅም ድህነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አንሰራርታለች ስንል ምኞት ሳይሆን ዛሬ በተጨባጭ ያረጋገጥነው እውነት ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የትውልድ አደራ፣ የሉዓላዊነት መገለጫ እና የኢትዮጵያውያን የጋራ ጽናት ማሳያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመረባረብ የአባይን ወንዝ ለመጠቀም ያደረጉትን ትግል፣ ያጋጠሟቸውን ተጽዕኖዎች እና የኩራት ታሪኮች አጠቃሎ የያዘ አዲስ መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
በታምሩ ደምሴ