ተናግሮ ማድረግ ፣ ቃል ገብቶ መፈጸም – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing ተናግሮ ማድረግ ፣ ቃል ገብቶ መፈጸም – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN መስከረም 8 /2018 ዓ.ም

የዘንድሮው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ተራ የቀን መቁጠሪያ ለውጥ ብቻ አይደለም። ሀገራችን አዲስ ገጽ ገልጣ አዲስ ታሪክ ጽፋለች፤ መርጣለች፣ መክራለች፣ አሸንፋለች፣ አንሰራርታለችም። ፈተናዎች ወደ ታላቅ ዕድል ተቀይረዋል።

በጸኑ እና ዝቅ ብለው በሠሩ ልጆቿ ጥረት የዘመናት የአዙሪት ጥላ ላይመለስ ተገፏል፤ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት ብቻ ለበርካታ አስርት ዓመታት ያላሳካናቸውን ድሎች ማሳካት ችለናል። ሩቅ የማለም፣ አቅዶ የመጀመር እና በፍጥነት የማጠናቀቅ አዲስ የሥራ ባህልም ገንብተናል። ይህ የሀገራችንና የመንግሥቷ ልዩ መገለጫ ሆኗል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚጨበጥ ብርሃን ፈንጥቋል። ከአፈሙዝ የሥልጣን ውርስ ተላቆ «ሀገረ መንግሥት በሕዝብ ካርድ ብቻ ይጽና» የሚል ድምፅ ከአጽናፍ አጽናፍ አስተጋብቷል። ሕዝባችን ቀን በፀሐይ፣ ሌት በውርጭ፣ ከሕመሙ ታግሎ፣ አትምረጥ ካለው ጋር ገጥሞ፣ የሚፈልገውን ነግሮናል። ሀገር አጽንቷል፣ ዴሞክራሲን መርጧል።

በሀገራዊ የምክክር ማዕቀፍ የኅብረ-ብሔራዊቷ ሀገራችን ልጆች ተሰባስበው ስለ እናት ሀገራቸው በአንድ አዳራሽ መክረዋል፤ ዘክረዋል። ይበጃል ያሉትን በጎ ሐሳቦች በነፃነት አቅርበዋል። በአጭሩ በኢትዮጵያ ምድር በዘመኑ አርበኞች አዲስ ገድል ተፈጽሟል። ይህ እውነት የልጆቻችንን ተስፋ ያለመለመ፣ በዘመናት መካከል በኩራት የምንተርከው ወርቃማ ታሪካችን ነው።

አንቆምም! ገና ብዙ ሥራ አለብን፤ እንፈጥናለን፣ መሰናክሎቻችንን ሁሉ በብሕላት እየዘለልን ወደ ሀገራችን መሻቶችና ሕልሞች በጽናት እንዘልቃለን። ታላቅ ሀገር አለችን፤ እየተማከርን እንገነባታለን፣ እየገነባንም እንማክራለን። ሁሉንም አሸናፊ ያደረገው አዲሱ መንገዳችን ይኸው ነው። መመካከር ።መመካከር ። መመካከር ።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሕግ የበላይነት በጥብቅ ዲሲፕሊን ከተመራበት መንገድ ጎን ለጎን፣ መንግሥታችን ያጠፉ ልጆቹን በምሕረት አቅፏል፤ በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን በይቅርታ ፈትቷል። ይህ ውሳኔ ብዙ ሀገራት የተመኙት፣ ኢትዮጵያ ግን ያሳካችው የበቀል አዙሪትን የሰበረ ታላቅ እርምጃ ነው።

ውሳኔው ለሀገራችን ዘላቂ ጥቅም ሲባል የተከፈለ ውድ ዋጋ መሆኑን የመደመር መንግሥት ይገነዘባል። ይቅርታ የጽኑ ሀገረ-መንግሥት ዋነኛ ምሰሶ ነው፤ ውሳኔው ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር ተጣጥሞ ብሔራዊ መግባባትን ያጠናክራል። የተፈቱት ወገኖቻችን ዕውቀታቸውን እና አቅማቸውን ለሀገር ግንባታ እንደሚያውሉ እናምናለን፤ ይህም ለነገዋ ኢትዮጵያ የማይናወጥ መሠረት ይጥላል።

ከፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ መግባባት ጎን ለጎን፣

በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ መረጋጋት እየተሻሻለ የሚመጣው በሀገር ደረጃ ጠንካራ የኢኮኖሚ ስኬቶች ሲመዘገቡ እና ሕዝባዊ አመኔታ ሲገነባ ነው። ኢትዮጵያ ይህን አድርጋዋለች።

ዛሬ ላይ በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካ ፈጣኑ እና መሠረቱ የሰፋ አስደናቂው እድገት ነው። ይህን እውነት ባንዳውም ባዳውም ሳይወድ በግዱ ይቀበለዋል።

የመደመር መንግሥት ጉርሷን የማትለምን እና ክብሯን የጠበቀች ሉዓላዊት ሀገር ለመፍጠር

በሁሉም መስክ ጥረት አድርጓል ።አበራታች ስኬቶች ተመዝግበዋል። ከለጋሽ እጅ ስንዴ የመጠበቅ ታሪካችን አብቅቶ በበጋ ስንዴ ራስን ከመቻል ያለፈ አዲስ ታሪክ ጽፈናል።

በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የራሳችንን ክብረ ወሰን ደጋግመን አሻሽለናል፤ በአካባቢ ጥበቃም ለዓለም አቀፍ ትብብር አርአያ ሆነናል። ይህ ስኬት በሌላ ሀገር የተፈጸመ ቢሆን ምንኛ በተነገረ ነበር፤ ዳሩ ግን እኛ ድልን ደጋግመን ያጣጣምን የጀግኖች አባቶቻችን ልጆች ነን። ፈጽመነዋል።

ርዕያችን ሩቅ ነው ፣ መንገዳችን መደመር ነው፣ ስንደመር አትርፈናል ፤ ስንሰባሰብ ጠንክረናል። በሌሎች ሀገራት የጸብ መንስኤ፣ የሀገር ዕዳ የሆኑትን ማዕድናት እኛ የሀገር ምንዳ ፣ የሀገር ተስፋ አድርገናል፤ በታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶቻችን ቀጣናውን አስተሳስረናል፤ የከተሞቻችን ገጽታ በዘመናዊ የኮሪደር ልማት ተለውጧል። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተስፋፍቷል ፤ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ገንበተናል።

ነባር ቅርሶቻችንንም አቧራቸውን አራግፈን ወደ ነገ አሻግርናል ።

ትውልድን አስበን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረግን ነው። የመንግሥት አሠራርንም ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ መሠረት ተጥሏል ። ከሁሉም በላይ ሀገራችንን ከሚሽኮረመም የውጭ ፖሊሲ አላቀን ለብሔራዊ ጥቅማችን በጽናት ቆመናል ፤ በአለም መድረክ የሚገባንን ጠይቀናል።

የምንገነባው ሀገረ-መንግሥት የመደመር እሳቤ ላይ የተመሠረተ ነው ፣ ትኩረቱም በጽኑ ተቋማት ግንባታ ላይ ነው። የፍትሕ፣ የፀጥታ እና የዴሞክራሲ ተቋሞቻችን ጠንካራ መሠረት ይዘዋል። ወገባችንን አጥብቀን ዝቅ ብለን በሠራነው ሥራ ቀና ብለን መሄድ ጀምረናል፣ ዛሬ ላይ ሀገር የሚሸከሙ፣ መጪውን ጊዜ የተለሙ እና ከሥርዓት መቀያየር የተሻገሩ ተቋማዊ አቅሞች ተፈጥረዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ የለውጡ መንግሥት ልዩ የሚያርገውን መገለጫን አስተዋውቋል፤ ፕሮጀክቶችን ይጀምራል፣ አጠናቆም ይመርቃል። ይህ በሕዝባችን አንደበት ተደጋግሞ የሚነገር እውነትኛ ምስክርነት ነው። የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ተከፍተዋል፤ ለዘመናት የኪሳራ ምሳሌ የሆኑ ተቋማት ወደ ትርፋማነት ተሸጋግረዋል ፤ በኢንቨስትመንት ፣በኤክስፖርት እና በተኪ ምርት እመርታዊ ለውጥ አሳክተናል።

ከዚህም በላይ ታላቁን የህዳሴ ግድባችንን ባጠናቀቅንበት ማግስት በጉባ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ እና የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል የሚወስኑ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለሕባችን አብሰረነዋል ።

የኢነርጂ ዋስትናን ለማረጋገጥ የኒውክሌር ማዕከል ለመገንባት አዲስ ውል ታስሮ ሥራ ተጀምሯል ፤ በሶማሌ ክልል የኢትዮጵያ ጸጋዎችን ገልጠናል። የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች ቀን ከሌት እየተሰራ ይገኛል ። በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን የሚያስተናግደው የቢሾፍቱ ኤርፖርት የአፍሪካ አቪዬሽን ዘውድ ደፍቶልን በሰማዩ ያነግሰናል።

በዓመት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያድነው የማዳበሪያ ፋብሪካም የግብርና ምርታማነትን በማረጋገጥ ለገበሬዎቻችን እፎይታ ይሆናል ፤ ተስፋችን ብዙ ነው። የብዙዎችን ህይወት የሚቀይረው የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ልማት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ሥራው ተጀምሯል። እናሳካዋለን ! ተናግሮ ማድረግ ፣ ቃል ገብቶ መፈጸም በመደመር መንግሥት ለትውልድ የተጣሉ ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review