አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ6 ከተሞች የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲኮችን ለማስተላለፍ ተስማሙ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ6 ከተሞች የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲኮችን ለማስተላለፍ ተስማሙ

AMN- መስከረም 8/2019 ዓ.ም

የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በስድስት ከተሞች የሚዘጋጁትን የ2019 የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ የስድስት ውድድሮች ተከታታይ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተመልካቾችና አዳማጮች ለማቅረብ አጋርነት ፈጥረዋል።

ይህ አጋርነት በ2019 የውድድር ዘመን በስድስቱም አስተናጋጅ ከተሞች የሚገኙ የሩጫ፣ የቱሪዝም፣ የህብረተሰብ እና የአካባቢ ባህል ታሪኮችን በስፋት ለማስተዋወቅ ያለመ ነዉ፡፡

ስምምነቱን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ እና የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ፈርመውታል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ( ኤ ኤም ኤን ) የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ ቋንቋዎችን በመጠቀም በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በህትመት እና በዲጂታል የሚያሰራጭ ሚዲያ እንደመሆኑ መጠን ይህንን ሰፊ ተደራሽነቱን እና አማራጭ ቻናሎቹን በመጠቀም፣ ከእያንዳንዱ አስተናጋጅ መዳረሻዎች ታሪኮችን፣ ልምዶችን እና እድሎችን በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ታዳሚዎች በማድረስ የልወቅሽ ኢትዮጵያን ውድድሮች ይደግፋል።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ፤ “አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አገር አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ በበኩላቸው፤ “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ይበልጥ ለማስተዋወቅና በክልል ከተሞች የምናዘጋጃቸውን ሩጫዎች ለህዝቡ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ይህ ስምምነት ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ የምዝገባ ሂደት መከፈቱንም ገልጸዋል፡፡

ይህ የስድስት ውድድሮች ተከታታይ መርሃ ግብር ሯጮችን፣ ጎብኚዎችን እና የባህል ወዳጆችን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ጥቂት ልዩ መድረሻዎች የሚያዟዙር ጉዞ ይሆናል።

የ2019 የውድድር ዘመን ተሳታፊዎችን ወደ ደብረ ብርሃን፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ በቆጂ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረር የሚወስድ ሲሆን ከሩጫ በላይ የሆነ ልምድ ያቀዳጃቸዋል።

እያንዳንዱ መድረሻ ልዩ የውድድር አጋጣሚን ከኢትዮጵያ የተለያየ ተፈጥሮ፣ የበለጸገ ባህል፣ ታሪክ፣ ምግብ እና ሞቅ ያለ እንግዳ ተቀባይነት ጋር አዋዝቶ ያቀርባል።

በጅራታ ቢየና

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review