AMN – መስከረም 13/2019 ዓ.ም
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1.6 ሚሊዮን በላይ የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውንና ከቱሪዝም ዘርፉ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል፡፡
የተገኘው ውጤት ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ300 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እና ከ21 በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ጭማሪ ማሳየቱን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።
የመስከረም እና የጥቅምት ወራት በርካታ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት በመሆኑ፣ የመሰረተ ልማት ዝግጅቶችን በማጠናከር የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በዓመት ከ30 እስከ 40 ይካሄዱ የነበሩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች፣ በተጠናቀቀው ዓመት ወደ 220 ማደጋቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመቀናጀትም በየዓመቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል የሚያልፉ ከ20 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ7 ቀን ነፃ የቪዛ እድል በመስጠት የእግረ መንገድ ቱሪዝምን ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል።