AMN- መስከረም 15/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠናከረ መከላከያ ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ፣ በየትኛውም መንገድ የአርበኝነቱን ሥራ ማረጋገጥ የሚችል፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ከምንም በላይ ከፍ አድርጎ የሚያይ እና የሚጠብቅ ሠራዊት አለው ሲሉ የሕግ እና አስተዳደር ምሁር ግርማ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በዚህም መንግሥት፣ ሠራዊቱ እና ሕዝቡ በተቀናጀ መንገድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል።
የሕግ እና አስተዳደር ምሁር ግርማ መኮንን (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ፤ የጸረ-ሰላም ኃይሎች ጥምረት ዋና ዓላማ ሕዝብን ማደናገር፣ በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ እንዲሁም መንግስትን ለማዘናጋት መሞከር ነው፡፡
አንደኛው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግሥት በማጠልሸትና የውሸት ትርክት በመፍጠር ሕዝቡን ማደናገር ሲሆን ሁለተኛዉ የሚዲያና የሌሎች አካላትን ትኩረት በመሳብ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር ነው።
እንዲሁም በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ህዝብ የመረጠውን መንግስት ለማዘናጋት መሞከር ሌላኛው ዓላማ ሲሆን መንግስት አሁን ባለበት ደረጃ የተደራጀ እና በእነዚህ እኩይ ተግባራት የሚደናገር አለመሆኑን አረጋግጠዋል።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተገኘውን ድል እንዲሁም ሌሎች በሀገሪቱ የተጀመሩትን ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች በማስተጓጎል የሀገሪቱን ብልጽግና ወደኋላ ለማስቀረት መሞከር ሌላኛዉ የጸረ-ሰላም ኃይሎቹ እኩይ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከተመሠረተች ጀምሮ በጠላቶቿ ያልተንበረከከች ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ምሁሩ፤ በተለይም በዓባይ እና በሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶቿ ምክንያት የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላቶች እንዳላረፉላት አብራርተዋል።
ጠላትነቱም የሌላውን ሀገር ድንበር ጥሶ በመሄድ ሳይሆን በገዛ ሀብቷና በራሷ ቤት የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሚንቀሳቀሱት የሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች የውጭ ተልዕኮ ተቀባዮች መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ግርማ፤ የእነዚህ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ጥምረት ሁለት አብረው የማይስማመሙ ሥልጣን ቢይዙ እንኳ ሀገር የመምራት ዝግጅትም ሆነ ብቃት የሌላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓባይ ላይ ለሺህ ዓመታት ያጣውን መብት አሁን በማግኘቱና የልማት ተስፋዉን አሳልፎ እንደማይሰጥና የትኛውም የጥፋት ኃይል መንግሥትንም ሆነ ሕዝብን ሊያደናግር እንደማይችል ምሁሩ አረጋግጠዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ