AMN- መስከረም 24/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ረጅምና ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች፡፡
የኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ከጥንታዊው ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈ ረጅም እና ውስብስብ ሂደት ነው፡፡
ያለፉት መንግስታዊ ሥርዓቶች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማትና ሰላም እንቅስቃሴዎች ውስጥ የየራሳቸው ጥንካሬ እና ውስንነት ቢኖራቸውም በተለይ በብሔረ መንግስት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ክፍተቶች መኖራቸውን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
በተለይ ከታሪክ እና ትርክት ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ከመኖራቸውም በላይ፣ እንደ ሀገር የጋራ የሆነ ብሔራዊ ትርክት በመገንባት ረገድ ውስንነቶች ነበሩ፡፡
ከማዕከላዊ መንግስትና ከክልሎች የኃይል ሚዛን ጋር በተያያዘም የመንግስት ሥልጣንን አግባብነት ባለው መልኩ ወደ ታችኛው የስልጣን እርከን ከማውረድና ከማስተዳደር አንፃርም እጥረቶች ነበሩ፡፡
ማዕከላዊው መንግስት ሲጠናከር ክልሎች ይዳከማሉ፤ በተቃራኒው ደግሞ ማዕከላዊ መንግስቱ ሲዳከም ሀገሪቱ ወደ መፈራረስ አደጋ ትገባለች የሚሉ ስጋቶች እንደነበሩም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የብሔር እና የዜግነት ፖለቲካ ውጥረት፣ የመንግስት ተቋማት ገለልተኛ አለመሆን፣ አካታች እና ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር አለመፈጠሩ እና ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ መረከብ የሚያስችል የፖለቲካ ባህል አለማዳበሩ በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ ውስጥ ከተስተዋሉ ውስንነቶች መካከል ዋንኞቹ ናቸው፡፡
ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር ከመፍታት ይልቅ፣ የኃይል እርምጃን ወይም ፖለቲካዊ ማግለልን መምረጥ ለዘመናት የቆየ የሀገረ መንግስት ስብራት ሆኖ መቀጠሉን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬም ከምትፈተንባቸው ዋንኛ የጸጥታ ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣንን በኃይልና በጉልበት ለመቀማት የሚደረግ ፍላጎት ሲሆን፣ ዛሬም እንደትናንቱ በጦርነት፤ በመጠፋፋት፤ በሴራና በተንኮል መንግስትን ገልብጠው ህዝብን ለመምራት የሚፈልጉ ኋለ ቀር ኃይሎች አሉ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህል፣ በህዝብ ብዛት፣ በተፈጥሮ ጸጋዎች፣ በስነምህዳራዊ አቀማመጥና በሌሎች ሀብቶች የታደለች ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ ያላት ሀገር ብትሆንም፣ በሀገረ መንግስት ግንባት ሂደት ውስጥ ያጋጠሟትን እነዚህንና መሰል ተግዳሮቶችን በሰለጠነ መንገድ መክሮና ዘክሮ የሚፈታ መንግስት መመስረት ባለመቻሏ ከጦርነትና ከድህነት አዙሪት መላቀቅ አልቻለችም፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ከኢትዮጵያ ያነሰ የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክና እድሜ ያላቸው አንዳንድ የዓለም ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠንካራ መንግስት፣ ሀገርና ኢኮኖሚ ከመገንባት አልፈው የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን በቅተዋል፡፡
በተለይ የለውጡ መንግስት ወደ አመራርነት ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያሉባትን የረጅም ዘመናት ውዝፍ ስብራቶች ለመጠገን ባደረገው ብርቱ ጥረት ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር፣ መንግስት በህዝብ ይሁንታና ምርጫ ብቻ እንዲመሰረት፣ የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነቶች በምክክር ብቻ እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡
ዋንኛ የሀገሪቱ የጸጥታ ችግርና የልዩነት መንስኤ የሆኑትን የታሪክ እና ትርክት ስብራት ለመጠገን በተከናወኑ መሰረተ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች የወል ትርክትን ለመገንባት የሚያስችሉ ጽኑ የመሰረት ድንጋዮች ተቀምጠዋል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነቱን አክብሮና አንድነቱን ጠብቆ የሚኖር ማህበረሰብ እየተገነባ በመሆኑ ብዝሃነት የግጭትና የጦርነት መንስኤ መሆኑ ቀርቶ የሀገሪቱ የልማትና የሰላም ጸጋ፣ ሀብትና ምሶሶ ለመሆን በቅቷል፡፡
የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌላውን ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት የሚያከብር፤ የሚቀበልና ከጥላቻ የጸዳ ትዉልድና ማህበረሰብ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡
የሰላምና የልማት ጸር ብቻ ሳይሆኑ እንደ ማህበረሰብ እና ሀገር አብሮ ለመኖር ሲያስቸግሩ የነበሩ ጽንፈኛ፣ ዘረኛ፣ ከፋፋይና አክራሪ እሳቤዎች በወንድማማችነት፣ አብሮነትና እኩልነት እሳቤዎች መተካት ጀምረዋል፡፡
ከተቋማት ግንባታ ጋር በተያያዘም ከፖለቲካዊ ሥርዓቶች ጋር የማይቀያየሩ፣ ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማትን ለመፍጠር የሚያስችሉ መሰረቶች ተጥለዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን ጨምሮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ መልክ እየተገነቡ ያሉት መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ብቻ ሳይሆኑ ኢኮኖሚውን የሚያሳልጡና ሀገርን የሚያሻግሩ ናቸው፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ለመጠፋፋትና ለመገዳደል የሚፈላለጉ፣ ስልጣን ቀረብኝ ብለው ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚተባበሩ ሳይሆኑ፣ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ከተመረጠው መንግስት ጋር ስልጣን ተጋርተው አብረው የሚሰሩና ለሀገራዊ ልማትና ሰላም በጋራ የሚቆሙ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን በሀሳብ የማሸነፍ አዲስ የፖለቲካ ባህል በመገንባት ላይ ሲሆን፣ የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነት እርግማን ሳይሆን በረከት እየሆነ መጥቷል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የልማት ስራዎች፣ ሁሉንም የሀገሪቱን ክፍሎችና ዜጎች ያሳተፉና ማዕከል ያደረጉ መሆናቸው ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል ፈጥሯል፡፡
ኢትዮጵያ በግብፅ፣ በሻዕቢያና ህገወጡ የህወሃት ቡድን ምክንያት ያጣችውን የባህር በር ለማስመለስ እያደረገች ያለው ብርቱ ጥረት የትናንትናውን የታሪክና የኢኮኖሚ ስብራት የሚጠግን ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ከመልክዓ ምድራዊ እስረኝነት ነጻ የሚያወጣ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው አዲሱ መንግስታዊ ሥርዓት ያለፉት ሥርዓቶች የፈጠሩትን በርካታ ስብራቶች የሚጠግንና የሚያክም፣ ለወደፊቱም መሰረት የሚጥል ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ልዕለ ኃያል ሀገር ሆና እንድትወጣ የሚያደርግ ርዕይ የሰነቀ ነው፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ