ሁለተኛው የሚድሮክ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር ጥቅምት 2 ይጀምራል

AMN- መስከረም 27/2019 ዓ.ም

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ሁለተኛው ሚድሮክ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር ከጥቅምት 2 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡

የሚድሮክ ሳምንትን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ኘሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሁናቸው ታዬ፣ በመስቀል አደባባይ በሚከፈተው ኤግዚቢሽንና ባዛር የገበያ ትስስር ከመፍጠር በተጨማሪ የሚድሮክ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ይሸጣሉ ብለዋል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ምርቶችን በማምረት ሀገርን ከማስጠራትና ከማልማት በተጨማሪ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በማለም በየዓመቱ ከሚያገኘው ትርፍ 10 በመቶውን ለዚሁ ተግባር እንደሚያውልም ጠቅሰዋል፡፡

በሁለተኛው ሚድሮክ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛርም በማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ላይ የሚያተኩር የፓናል ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አሁን ላይ ከ45 በላይ ኩባንያዎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በሆስፒታሊቲ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽንና ሪልስቴት ዘርፎቹ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ እድል የፈጠረ ግዙፍ ተቋም መሆኑን አቶ ሁናቸው ተናግረዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በታማኝ ግብር ከፋይነት ግንባር ቀደም ሲሆን፣ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ብቻ ከ31 ቢሊየን ብር በላይ ግብር በመክፈል ታማኝ ግብር ከፋይነቱን በተግባር ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ሚድሮክ ራሱ አምርቶ ለውጭ ገበያ ባቀረበው ምርት ከ390 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱንም ጠቅሰዋል፡፡

አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ወደ ስራ በማስገባት፣ በቀጣይ ለሚካሄደው ኮፕ 32 አዳዲስ ሆቴሎችን እየገነባ እንደሚገኝ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review