AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም
የትግራይ ወጣቶች የመሣሪያ ቃታ ከመሳብ ይልቅ ወደ ልማት፣ ትምህርትና ሥራ ሊመለሱ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በትግሪኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ እርስ በእርስ የሚደረግ ውጊያ አሸናፊ እንደሌለውና በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በመጠቆም ፣ በተለይም ለባዕዳን ኃይሎች ጥቅም የሚደረግ ውጊያ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸዋል።
በቅርብ ጊዜያት በነበሩ ውጊያዎች የደረሰው ጉዳት አሳዛኝ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የቀጠለው ውጊያ ዋነኛ ሰለባ ወጣት መሆናቸውንና ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ወጣት ሕይወቱን ማጣቱን ፣ አካሉ መጉደሉንና ለስነ-ልቦናዊ ችግር መዳረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም ክላሽንኮቭ ታጥቆ ሲንከራተት የነበረው ብዙ ወጣት ወደ ሥራው መመለስና በመልሶ ግንባታ ላይ መሳተፍ አለበት ብለዋል።
ተገደው ወደ ጦርነት የገቡና ገና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ላልተመለሱ ወጣቶች መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ፣ የሕወሓት አመራሮች ላለፉት 50 ዓመታት ሲዋጉ ቢቆዩም ራሳቸው እንደማይሞቱና እንደማይቆስሉ ገልጸዋል።
አመራሮቹ ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ከመላካቸውም በላይ በወርቅ ንግድና በሕንፃ ግንባታ ተሰማርተው የተመቸ ሕይወት እየኖሩ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ እነሱ ተንደላቀው ሲኖሩ አንተ ለምን ትሞታለህ፣ ትቆስላለህ? ሲሉ ወጣቱ እራሱን እንዲጠይቅ አሳስበዋል።
ሕይወትህ የራስህ እንጂ የድርጅት ወይም የድርጅት መሪዎች አይደለችም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ወጣቱ ለእናቱ፣ ለአባቱና ለትግራይ ሲል ሕይወቱንና አካሉን ጠብቆ ለልማት ማዋል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የወጣቱ ቦታ በዩኒቨርሲቲ፣ በንግድ፣ በእርሻና በፋብሪካዎች ውስጥ መሆን እንደሚገባው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ እጅህ የጠመንጃ ቃታ ከመሳብ ይልቅ ኮምፒውተር ላይ መዋል አለበት፤ በመሆኑም ክላሽንኮቭህን አስቀምጠህ ወደ ልማትህ ተመለስ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በታደሰ ሽፈራው