AMN – ኅዳር 16/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በብዝኃ-ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት ከሰጠቻቸው አምስት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።
በዚህም መሠረት በቅርብ ዓመታት በአዲስ አበባ የተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎች እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋን እንደ ስሟ ውብና ለጎብኚዎች ምቹ አድርገዋታል።
የእንጦጦ ተራራን ወደ ዘመናዊ የስፖርት፣ የባህልና የመዝናኛ ማዕከል የቀየረው የእንጦጦ ፓርክ፣ ሰው ሠራሽ ሐይቅንና የውኃ መብራት ትዕይንትን ያቀፈው የወዳጅነት አደባባይ፣ የወደፊቱን ቴክኖሎጂና ፈጠራ የሚያሳየው የሳይንስ ሙዚየም፣ እንዲሁም የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን ታሪክ በዘመናዊ መልኩ የሚዘክረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ የከተማዋ አዳዲስ ድምቀቶች ናቸው።
በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የቀበና ወንዝ ዳርቻ እና ግድብ ፕሮጀክትም ሌላኛው የመዲናዋ መስህብ ሆኗል።
እነዚህ ልማቶች ቀደም ሲል በከተማዋ ይስተዋል የነበረውን የመዳረሻ ስፍራዎች እጥረት በመቅረፍና የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ አራዝመዋል፤ ለኢኮኖሚውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በመዳረሻዎቹ ግንባታ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በሆቴል፣ በትራንስፖርት፣ በአስጎብኚነት እና በባህል ምግብ ቤቶች ለተሰማሩ በርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
ይህም ዓለም አቀፍ የሆቴል ብራንዶችና የግል ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
እነዚህ ስፍራዎች ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ኤግዚቢሽኖችን የመሳብ አቅምን አሳድገዋል።
ለጉባኤ የሚመጡ መሪዎችና ዲፕሎማቶች ከስብሰባ በኋላ የሚጎበኟቸው ታሪካዊና ዘመናዊ ስፍራዎች መኖራቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትንና የባህል ልውውጥን አጠናክሯል።
የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን የማበረታታት ሥራም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ የዜጎችን አብሮነት ለማጎልበት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
የመዳረሻዎች ልማት ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ትልቅ ዕድል ሰጥቷል።
ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ሀገራዊ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገው መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ይህም አዲስ አበባን በከተማ ልማትና በዲፕሎማሲ ለሌሎች ሀገር ከተሞች ተሞክሮ የምታካፍልበት እና በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪዝም ማዕከል የምትሆንበት ደረጃ ላይ አድርሷታል።
በበረከት ጌታቸው