AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም
በ2017 በጀት ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘጋጀውን የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መርቀው ከፍተዋል።
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የምርትና አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቀርፆ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ወደስራ በማስገባት በተቀመጠላቸው ጊዜ እና ጥራት በመገንባት ስኬታማ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱንም አስታውቀዋል።
የወርቅ እና ቡና ምርቶችን ጨምሮ ግብርና፣ ማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርትና አገልግሎቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።