ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ከ1ሺህ 980 በላይ የትምህርት ባለሙያዎች በነገው ዕለት ያስመርቃል።
ዩኒቨርሲቲው “ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ” በሚል ስሙ እና አዲስ በተሰጠው ተልእኮ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስተምራቸው የቆየውን የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችንም ያስመርቃል፡፡
የቀድሞው የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ የትምህርት አመታት በተለያዩ የትምህርት መስኮች በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ማፍራት የቻለ ብቸኛው የትምህርት ዪኒቨርስቲ ነው፡፡
ዪነቨርስቲው ከአመት አመት ራሱን እያሻሻለና የተለያዩ የትምህር መስኮችን እየጨመረ በርካታ ተማሪዎችን ለውጤታማነት አብቅቷል፡፡
በአምስት ፕሮግራሞች ማለትም በድግሪ 333፤በማስተርስ 706፤በዲፕሎማ 181፤በ.ፒ.ጂ.ዲ.ቲ 763 እና በፒ.ኤ.ች ዲ 6 በድምሩ 1989 የትምህርት ባለሙያዎችን በነገው ዕለት እንደሚያስመርቅ የዪንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በፒ.ኤ.ች ዲ ደረጃ ተመራቂዎችን ማካተቱ የነገውን ምረቃ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የተለየ እንደሚያደርገው ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል፡፡ ውቅቱን የሚመጥን የትምህርት ዩኒቨርስቲ ለመሆንም ትምህርት ሚኒስቴር፣ገንዘብ ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ማድረግ ችለዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣትም ከከተማ አስተዳደሩ 16 ሄክታር መሬት መረከቡን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“የበቃ መመህር የበቃ ትውልድ ያፈራል” በሚል መርህ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የእቅም ግንባታ ስራ እና ምርምሮችን ጨምሮ የማስፋፊያ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡
በሚካኤል ህሩይ