AMN- ጥር 21/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባን የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ሐገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሁሉ አቀፍ ስራዎች በጀትን በአግባቡ ለታለመለት አለም ማዋል አበርክቶው የጎላ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2018 በጀት አመት አጋማሽ የኦዲት ፎረም ጉባኤ ተካሒዷል።
በጉባኤው ከታላለቅ ተቋማት እስከ ወረዳ ባሉ ተቋማት በ2012 እና 2013 ዓ.ም የተገኙ የኦዲት ግኝቶች እና የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችን በመዳደስ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን ማስቀመጥ ላይ ትኩረት ተድርጓል።
አዲስ አበባ ከተማ የገቢ አቅሟን በማሳደግና በማዘመን የመደበኛን ካፒታል በጀቷን በራሷ አቅም መሸፈን ችላለች ያሉት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና፤ ሐገራዊ ጥቅም ያላቸው ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግና መዲናዋን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎች የመንግስትና የህዝብ ኃብት ለታለመለት አላማ እንዲውል የክትትልና ቁጥጥር ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የህዝብና የመንግስት ኃብትን ከብክነት በመታደግ ለታለመለት አላማ እዲውል የክትትልና ቁጥጥር ስራን የሚሰሩ ገለልተኛ ተቋማትን ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፤ በዚህም በ2012 እን 2013 በተደረገ የኦዲት የማጥራት ስራ ከተገኘ 2.3 ቢሊየን ብር ውስጥ ከ1.1 ቢሊየን ብር እንዲመለስ ማድረግ ስለመቻሉም ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከብክነት የጸዳን ስራ በመስራት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ያሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የፎረሙ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ የመንግስትን ሐብት ህዝብን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ስራዎች ለማዋል ተጠያቂነትን እያሰፈኑ የመጓዝ ስራ ተጠናክሮው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በመድረኩ በ2012 እና 2013 ዓ.ም በተደረገ የኦዲት ማጣራት ስራ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለወሰደው የእርምት እርምጃና ላሳየው ቁርጠኝነት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶለታል።
ሚዲያው በህዝብና መንግስት መካከለው ሁነኛ ድልድይ ከመሆን ባሻገር ጠንካራ የውስጥ አደረጃጀትን በመፍጠር በጀቱን ለተገቢው አላማ በማዋልና ራሱን ከኦዲት ግኝት ነጻ በማድረግ በኩል አበረታች ስራ ስለመስራቱ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ ራሳቸውን ከኦዲት ግኝት ነጻ ላደረጉ ተቋማት የማበረታቻ እውቅና ተበርክቷል።
በሄኖክ ዘነበ