AMN የካቲት 14/2018
“አዲስ አበባ ካሰብኩት በላይ ሆና አገኘኋት፤ ይህች ኢትዮጵያ መሆኗን ለማመን ተቸገርኩ” በማለት በዩቲዩብ ገጿ ላይ ያጋራችው ኬሪ ፓትሳሊስ፣ ከ160 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሏት ታዋቂ ግለሰብ ናት።
ኬሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞችን በመዘዋወር የምትጎበኝ ሲሆን፣ በምርጥ የዓለም ከተሞች ውስጥ የሚያጋጥሟትን አስገራሚ ነገሮች ለተከታዮቿ ታጋራለች።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በነበራት ቆይታ ያየችው የከተማ ልማት እጅግ እንዳስደመማት ገልጻለች። “በዚህ ጉዞዬ ያልጠበቃችሁትንና አዲስ ነገር አሳያችኋለሁ” በማለት ጉብኝቷን ትቀጥላለች።

አዲስ አበባ “አጃኢብ” የሚያሰኝ እድገት ላይ ትገኛለች በማለት አድናቆቷን የገለጸችው ፓትሳሊስ፣ ባረፈችበት ሆቴል ከተደረገላት አቀባበል ጀምሮ በመንገዶቿና በከተማዋ ልማት “በጣም ውብ ነው” ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች።
ከሚቀርብላት ምግብ ጀምሮ እስከ ምቹው የኢትዮጵያ አየር ንብረት ድረስ ሁሉም ነገር እንደተመቻት አረጋግጣለች።
ከመጣችበት አገር ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጠቀሰችው ፓትሳሊስ፣ በአዲስ አበባም የኤሌክትሪክ መኪኖች በዚህ መጠን ይበዛሉ ብላ እንዳልጠበቀች በከተማ ጉብኝቷ ወቅት ገልጻለች።

ፓትሳሊስ ኢትዮጵያ በታሪኳ በማንም ያልተገዛች አገር መሆኗን በማንሳት፣ የአፍሪካ አገራት በየዓመቱ ስለወደፊት እጣ ፈንታቸው ለመምከር በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤት እንደሚሰበሰቡ ገልጻለች።
ኬሪ ፓትሳሊስ በዚህ ብቻ አላበቃችም፤ ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትም በመሄድ “አዲስ አበባ እንዲህ ያማረችው በአንድ ሌሊት አይደለም” በማለት፣ በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመዝናናት የቀድሞ መሪዎችን ታሪክ አስታውሳለች።
በተለይም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይሰበስቧቸው የነበሩ ውድ መኪናዎችና ባቡሮችን ስትመለከት “እንዴት ያምራሉ!” በማለት ጎብኝታለች።
የ24/7 የሥራ ባህል አዲስ አበባን አስውቦ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ልብ እንዲማርክ ማድረጉን ቀጥሏል፤ አዲስ አበባ ነገ ከዛሬው በበለጠ ለመዋብ ሰፊ ዕድል አላት ስትልም ገልጻለች፡፡
በመልካሙ አበበ