AMN – የካቲት 15/2018 ዓ.ም.
የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በሐዋሳ ከተማ ተካሒዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ምስረታ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ማግስት ሠራዊቱ የማንኛውም ብሔር፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለው ሀገራዊ ሠራዊት ሆኖ እንዲገነባ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የመካናይዝድ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር፣ የሳይበር ኃይሎች ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት የምድርና የባሕር ኃይል ብቁ ሠራዊት ግንባታ ተከናውኗል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጆች የተሰባሰቡበት፣ ለማንኛውም የውጭም ሆነ የውስጥ ጥቃት የማይበገር፣ ዘመናዊና ፕሮፌሽናል ሠራዊት ሆኖ እንዲደራጅ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ የዛሬው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ምስረታም የዚሁ የሪፎርም ውጤት እና ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ዕዝ በልዩ ስልጠና እና በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጀ ሆኖ፣ ሀገርን ከማንኛውም ዓይነት ስጋት ለመከላከል ዝግጁ ሆኖ ስለመገንባቱም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በቆራጥነትና በታማኝነት የሀገሩን ሰላም ለማስከበር የሚያደርገውን ተጋድሎ ሁላችንም ልናደንቀውና ልንደግፈውም ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሚካኤል ኅሩይ