ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ ኔትወርክ የሚያገኘውን የሕዝብ ሽፋን ወደ 95.5 በመቶ ከፍ የሚያደርግ ስምምነት ተፈራረም

You are currently viewing ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ ኔትወርክ የሚያገኘውን የሕዝብ ሽፋን ወደ 95.5 በመቶ ከፍ የሚያደርግ ስምምነት ተፈራረም

AMN – የካቲት 30/2018 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም ግዙፍ የኔትወርክ ማስፋፊያ እና የማዘመን ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነትን ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ዜድ.ቲ.ኢ (ZTE) ጋር በባርሴሎና ተፈራሟል።

ከ”2026 የሞባይል ዓለም አቀፍ ኮንግረስ” ጎን ለጎን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩና የኩባንያው ከፍተኛ የማኔጅመንት አመራሮች ከዜድ.ቲ.ኢ (ZTE) ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ስትራቴጂያዊ ስምምነቱን አከናውነዋል።

ስምምነቱ 115 የገጠር ጣቢያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 647 የኔትወርክ ጣቢያዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ የኔትወርክ ተደራሽነት ለማሳደግ እና የኢትጵያን የዲጂታል አካታችነት ይበልጥ ለማስፋፋት የላቀ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የ4ጂ ኔትወርክ የሚያገኘውን የሕዝብ ሽፋን ወደ 95.5 በመቶ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ዘመናዊ የሞባይል ብሮድባንድ ኢንተርኔትን አገልግሎቱ ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች በማድረስ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያፋጥናል።

ስምምነቱ አስተማማኝ እና ለወደፊት ዝግጁ የሆነ የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት በመዘርጋት የዜጎችን፣ የተቋማትን እና የቢዝነሶችን አቅም ለመገንባት በመሆኑ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የዲጂታል ማዕከል ለመሆን ለምታደርገውን ጉዞ ወሳኝ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review