AMN — መጋቢት 19/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በዘላቂነት ለመቅረፍ እና የከተማዋን መሰረተ ልማት ለማዘመን የታለሙ የቴክኖሎጂ ስራዎች በስፋት እየተተገበሩ ይገኛሉ።
ከእነዚህም መካከል በቴዎድሮስ አደባባይ ፊት ለፊት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመናዊው “ስማርት ፓርኪንግ” አንዱ ሲሆን፤ ማዕከሉ አሽከርካሪዎች መኪናቸውን ለማቆም የሚባክንባቸውን ጊዜና ጉልበት የሚቀንሱ የላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያካተተ ነው።
በዘርፉ የተሰማራው የፊትኮም ኢንጂነሪንግ ማኔጀር ወ/ት በእምነት ተፈሪ እንደገለጹት፣ በእያንዳንዱ የፓርኪንግ ሎት ላይ የተገጠሙ የካሜራ ሴንሰሮች የመኪናውን የሰሌዳ ቁጥር በማንበብ መኪናው የት ቦታ ላይ እንደቆመ በዲጂታል መንገድ ይመዘግባሉ።
በተጨማሪም አሽከርካሪዎች በፓርኪንግ ስፍራው ውስጥ በቀላሉ ቦታ እንዲያገኙ ለማስቻል አረንጓዴ መብራት ቦታው ክፍት መሆኑን፣ ቀይ መብራት ደግሞ ቦታው መያዙን የሚጠቁሙ ግልጽ ምልክቶች መመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ የፓርኪንግ ፈቃድና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ላፈሳ በበኩላቸው፤ አሽከርካሪዎች ባሉበት ሆነው በ”Driver App” የሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት የትኛው የፓርኪንግ ቦታ ክፍት እንደሆነና ያለውን የቦታ ብዛት አስቀድመው ማወቅ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ይህም መኪና ማቆሚያ ፍለጋ የሚባክን ጊዜን እንደሚያስቀር አመልክተዋል።
በከተማዋ የሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው የሚከሰተው አሽከርካሪዎች የመኪና ማቆሚያ ፍለጋ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ስማርት ፓርኪንጉ ትልቅ መፍትሄ መሆኑን ገልፀዋል።
ከቴክኖሎጂው ዝመና ጎን ለጎን የተከናወነው የኮሪደር ልማትም በከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እና በሰው ህይወት ደህንነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
ቀደም ሲል በመንገድ ዳርቻዎች ላይ ይደረግ የነበረው መኪና የማቆም ልምድ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የመንገዶችን የትራፊክ ፍሰት ማሻሻል መቻሉም ቡድን መሪው ገለጸዋል።
ይህ የተቀናጀ አሰራር አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ደህንነቷ የተጠበቀ እና ዘመናዊ ዓለም አቀፍ ከተማ ለማድረግ እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ጥረት አካል መሆኑ ተመላክቷል።
በበረከት ጌታቸው