AMN-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
ከነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራስፖርት ተጠቃሚዎች ቁጥሩ በቀን ከ53 ሺህ ወደ 70 ሺህ ከፍ ማለቱን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሮቤ መንገሻ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደተናገሩት ባለፉት 15 ቀናት ከነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ፍላጎት በመጨመሩ በቀን እስከ 70 ሺህ ለሚደርሱ ተጠቃሚዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት በቀን በአማካይ 18 ባቡሮችን በማሰማራት ከ 13 ሚሊየን ለሚበልጡ ተሳፋሪዎች የባቡር ትራንስፖርት መስጠት መቻሉን እና ከትኬት ሽያጭ ከ257 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገባት መቻሉንም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
ተሳፋሪዎች ቤታቸው ሆነው ትኬት በዲጂታል ክፍያ በቴሌ ብር የሚገዙበትን አሰራር በአምስት የባቡር ጣቢያዎች ላይ መጀመሩን የገለጹት ኃላፊው 10 የባቡር የትኬት መቁረጫ ሱቆችን ወደ ባቡር ስቴሽን ፕላትፎርም ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡

ከነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ታሪፍ ሲጨምር የቀላል ባቡር ታሪፍ ባለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም ተሳፋሪዎች ካሉት የትራንስፖርት አማራጮች ከሀያት እስክ ጦርሃይሎች 20 ብር ይከፍላሉ ፡፡
የባቡር አገልግሎቱ በአንድ ጉዞ ከ250 እስክ 300 ሰዎችን የሚይዝ በመሆኑ በነዳጅ እጥረት ምክንያት በመዲናዋ ለሚከሰት የትራንስፖርት እጥረት መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ