በመዲናዋ የተከፈቱ የበዓል ባዛሮች ለሸማቾች እፎይታን የሰጡ ናቸው

You are currently viewing በመዲናዋ የተከፈቱ የበዓል ባዛሮች ለሸማቾች እፎይታን የሰጡ ናቸው
  • Post category:በዓል

AMN-ሚያዚያ 3/2018ዓ.ም

የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የተከፈቱ የንግድ ባዛሮች፣ ሸማቾች የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

ኤ ኤም ኤን ቅኝት ባደረገበት ጉለሌ ክፍለ ከተማ የተከፈተው ባዛር ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን በመከላከል ለነዋሪዎች አማራጭ የገበያ ስፍራ ሆኗል።

በባዛሩ የተገበያዩ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በባዛሩ የሚቀርቡ ምርቶች ከወትሮው የሱቅ ዋጋ ጋር ሲነጻጸሩ በእጅጉ ቅናሽ የታየባቸው ናቸው።

በባዛሩ ከተገበያዩት መካከል ወይዘሮ ህይወት ለገሰ እንደሚሉት ፣ የሽንኩርትና የቅቤ ምርቶችን በአቅራቢያቸው ማግኘታቸው የትራንስፖርት ወጪን ከማዳኑ ባለፈ ጥራት ያለው ምርት እንዲሸምቱ አስችሏቸዋል።

ሌላኛው ሸማች አቶ እሸቱ ወልዴ በበኩላቸው፣ መሰል የገበያ አማራጮች መኖራቸው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው ማህበረሰብ ትልቅ እፎይታ መሆኑን ገልጸው ፣ መንግስት በየወረዳው እንዲህ ያሉ የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋቱ ምስጋና አቅርበዋል።

ሰብለ ደሳለኝ የተባሉ ሸማችም የሚፈልጉትን እንደ ሽንኩርት እና እንቁላል የመሳሰሉትን በአንድ ቦታ ማግኘታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በዓልን ጠብቆ እንደዚህ አይነት ገበያዎች መዘጋጀታቸው እውነት ለመናገር ለደሀው ህብረተሰብ ምቹ ነው የሚሉት አቶ አለማየሁ ሽፈራው ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም ህብረት ስራ ማህበራት የሚያቀርቧቸው ምርቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በገበያው ላይ መረጋጋት መፍጠሩን ነው ሸማቾቹ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹት፡፡

በባዛሩ ምርታቸውን የሚያቀርቡ ነጋዴዎችም ለበዓሉ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በአትክልት ንግድ የተሰማሩት አቶ ዘነበ ጌታቸው እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የሽንኩርት ምርት በከፍተኛ መጠን እየቀረበ ይገኛል። ጥሩ ጥራት ያለው ሽንኩርት ማቅረባቸውንና ገበያውም በጣም የተረጋጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ነጋዴ አቶ ዘካሪያስ ሲሳይ በበኩላቸው፣ ምርቶችን በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሸማቹን ለማገልገል እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፣ የገበያ ትስስሩ ለነጋዴውም ሆነ ለሸማቹ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

ሸማቾች በበዓላት ወቅት የሚዘጋጁ መሰል የንግድ ትርኢቶችና ባዛሮች በወቅታዊነት ብቻ ሳይወሰኑ፣ ተጠናክረውና ተከታታይነት ባለው መልኩ እንዲቀጥሉ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

በታደሰ ሽፈራዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review