ፈረንሳይ ከአፍሪካ ጋር ወዳጅነቷን ለማደስ ቁርጠኝነቷን አሳየች

You are currently viewing ፈረንሳይ ከአፍሪካ ጋር ወዳጅነቷን ለማደስ ቁርጠኝነቷን አሳየች

AMN — ግንቦት 4/2018 ዓ.ም

ፈረንሳይ ለዘመናት በምዕራብ አፍሪካ ቅኝ ግዛቶቿ ላይ የነበራት ተፅዕኖ እየተሸረሸረ፣ ወታደሮቿ እየተባረሩና ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ እየላላ በመጣበት ወቅት፤ ፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮን በናይሮቢ በመገኘት ከአፍሪካ ተስስር ለመፍጠር አዲስ መንገድ ጀምረዋል።

ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተሳተፉበትና ለሁለት ቀናት በሚቆየው የ”አፍሪካ ፎርዋርድ” ጉባኤ ላይ ፈረንሳይ ይህን መሰል መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገር ማካሄዷ ብቻውን ትልቅ ፖለቲካዊ ምልክት እንደሆነ ፍራንስ 24 ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን ጉባኤው በአፍሪካ ውስጥ የ23 ቢሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንት ማንቀሳቀሱን ገልጸው፤ ይህ ውጤት ፈረንሳይ ከአህጉሪቱ ጋር የ”አቻ ለአቻ” ግንኙነት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ማስረጃ ነው ብለዋል።

በጉባኤው አፍሪካ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ብድር ለመውሰድ የምትከፍለው ወለድ ከሌሎች ክፍላተ ዓለም ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ ተመጣጣኝ አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ የብድር ደረጃ መመዛኛ ተቋማት አፍሪካን “ከፍተኛ ተጋላጭነት” እንዳላት አድርገው መፈረጃቸው እንደሆነ ፕሬዝዳንት ሩቶ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በበኩላቸው ቅሬታውን በመቀበል፣ ለአፍሪካ ኢንቨስትመንቶች “የመጀመሪያ ኪሳራ ዋስትና ሥርዓት” እንዲፈጠር እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

ይህ አሰራር ወደ አህጉሪቱ የሚፈሰውን የግል ካፒታል መጠን ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል።

በአፍሪካ ፎርዋርድ ጉባኤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና የንግድ ድርጅት መሪዎች ታድመዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review